ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን ልታባርር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ ሱዳን በህገወጥ መንገድ ገብተዋል ያለቻቸውን ከ20 በላይ የውጭ ዜጎች በአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞችን እንደምታባርር አስታወቀች።
ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ከቀናት በፊት ጁባ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በደረሱበት ወቅት ሲሆን ፓስፖርትም ሆነ የጉዞ ሰነድ ሳይኖራቸው ወደ ደቡብ ሱዳን ገብተዋል ተብሏል።
እነዚህ ስደተኞች መነሻቸውን ከሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ያደረጉ ሲሆን ደቡብ ሱዳንም የገቡት ደህንነት ፍለጋ ነው ተብሏል።
ከካርቱም ተነስተው ከቤንቲዩ ወደ ጁባ እንዲሁም በሰሜን ደቡብ ሱዳን ፓሎች ከተማ የአገር ውስጥ በረራዎች ማድረጋቸውን የደቡብ ሱዳን የኢሚግሬሽን ባለስልጣን ተናግረዋል።
የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢሚግሬሽን ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል አተም ማሮል ቢያር ግለሰቦቹ ወደመጡበት እንደሚመለሱ ተናግረዋል። ስደተኞቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የጉዞ ሰነድ ስለሌላቸው ወይም በደቡብ ሱዳን ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ስላልነበራቸው ነው ብለዋል።
“ከተለያዩ አገሮች የሚመጡና የጉዞ ሰነድ የሌላቸውን መንገደኞች መቀበላችንን መቀጠል እንችልም። የጉዞ ሰነድ ለምን እንደሌላቸው ምክንያቱን ስለማናውቅም አገራችንን አደጋ ላይ ይጥላል” ሲል የሃገር ውስጥ ጋዜጣ ዘ ዳውን ሌተናል ጄኔኔራል ቢያርን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በተያያዘ ዜና ኡጋንዳም ከሳምንት በፊት 186 ህገወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሏን አስታውቃለች። ከነዚህ ስደተኞች ውስጥ አምስት ኢትዮጵያውያንና 116 ኤርትራውያን እንደሚገኙበትም የኡጋንዳ ኢሚግሬሽን ቁጥጥር ገልጿል። በርካቶቹ እነዚህ ስደተኞች የጉዞ ሰነዶች እንደሌላቸው የተጠቀሰ ሲሆን የተወሰኑት ደግሞ ቪዛቸው እንዲሁም የስራ ፈቃዳቸው ቀን ያለቀበትና ከተፈቀደላቸው ስራ ውጭ እየሰሩ የነበሩ እንደሆነም ተጠቁሟል። ስደተኞቹ በህገወጥ መንገድ በአገሪቱ በመቆየታቸውም ቅጣት ይጠብቃቸዋል ተብሏል።
ስደተኞቹ በጁባ በሚገኘውና ለውጭ ሃገር ዜጎች ማቆያ በሆነው ኮሎሎ በተሰኘው ልዩ የኢሚግሬሽን ተቋም እንዲቆዩ የተደረጉ ሲሆን ከአገር እስኪወጡም በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም የሃገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
የነዳጅ ዘይት አምራች የሆነችው ደቡብ ሱዳን በምስራቅ አፍሪካ ለንግድ የሚመጡ የብዙ ስደተኞች መዳረሻ ናት። ነገር ግን ከድንበሯ የተነሳ በህገወጥ መንገድ የሚጎርፉ ስደተኞችን ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖባታል።












