በብራዚል ግራ ዘመሙ ሉላ እና ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ለሁለተኛ ዙር ምርጫ ተፋጠዋል

የምረጡኝ ቅስቀሳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በብራዚል ምርጫ ግራ ዘመሙ ሊዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ እና በስልጣን ላይ ሚገኙት ቀኝ ዘመሙ ጃየር ቦልሶናሮ ለሁለተኛ ዙር ምርጫ ተፋጠዋል።

የመጀመሪያው ዙር የምርጫ ውጤት ተቆጥሮ ሊጠናቀቅ ጥቂት የቀረው ሲሆን ሉላ 48 በመቶ ድምጽ በማግኘት ይመራሉ። ቦልሶናሮ በ 43 በመቶ ድምጽ ይከተላሉ። ውጤቱ ቀደም ሲል ከህዝብ አስተያት ከተሰበሰበው ይለያያል ተብሏል።

ሉላ የሚያስፈልጋቸውን ከ50 በመቶ ድምጽ በላይ በማግኘት ሁለተኛ ዙር ምርጫ እንዳይከናወን ማድረግ አልቻሉም።

መራጮች ከሁለቱ ዕጩዎች ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ውሳኔ ለማስተላለፍ አራት ሳምንታት ይጠብቃሉ።

በብራዚል ምርጫ በመጀመሪያው ዙር የሚያስፈልገውን ውጤት በማግኘት ምርጫውን ማሸነፍ ከባድ ሲሆን ይህን ማሳካት የተቻለው ከ24 ዓመት በፊት ነው።

ሁለቱም ዕጩዎች ውጤታቸውን እንደድል እንደሚቆጥሩት ይጠበቃል።

በአውሮፓውያኑ 2018 ምርጫ ወቅት ከሙስና ጋር በተያያዘ ማረሚያ ቤት ለነበሩት ሉላ የአሁኑ ውጤት ትልቅ ስኬት ነው።

በህዝብ አስተያየት ከተቀናቃኛቸው ርቀው ለነበሩት ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ ደግሞ ውጤቱ ተፎካካሪነታቸውን ያሳዩበት ነው።

ሁለቱ ዕጩዎች ለዓመታት ሲንከባለል ከቆየው ተፎካካሪነታቸው በኋላ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የስድብ ቃላት ሲወራወሩ ቆይተዋል።

ሉላ ለ580 ቀናት ሉላ ማረሚያ ቤት ካሳለፉ በኋላ ነጻ የተባሉበትን ጉዳይ በማስታወስ ቦልሶናሮ ከምርጫው በፊት በነበረው የቴሌቭዥን ቅስቀሳ ተፎካካሪያቸውን "ሌባ" ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

ሉላ ደግሞ በምላሹ ቦልሶናሮን "እብድ" ሲሉ ሰድበዋቸዋል።

የሁለቱ ጉዳይ ወደ ህብረተሰቡም ተዛምቷል።

ከምርጫው በፊት በነበረው ምሽት የሪኦ ነዋሪዎች “ሉላ ሌባ ነው” እና “ከቦልሶናሮ ጋር ልቀቁ” በማለት ርስ በእርስ ቃላትን ተወራውረዋል።

ሁለቱ ዕጩዎች በአካሄድ ላይም በተቃራኒ የቆሙ ናቸው።

ሉላ የአማዞን ደንን ለመጠበቅ ቃል ሲገቡ ቦልሶናሮ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው በማለት እንጠቀምበታለን ብለዋል።

ብዙ ብራዚላዊያን ግን እንደ ምግብ ዋጋ መጨመር ያሉ ብዙ ጥያቄዎች አሏቸው።

በሃገሪቱ ያለው የሃብት ልዩነት ላይ አዲሱ ፕሬዝዳንት እንዲሠሩም ይፈልጋሉ።

ቦልሶናሮ “ፈጣሪ ብቻ ነው” ከወንበሬ የሚያነስነሳኝ ማለታቸውን ተከትሎ ውጤቱን ላይቀበሉ ይችላሉ የሚለው ርዕሰ ጉዳይ ነበር ከምርጫው በፊት ትልቅ መወያያ የነበረው።

የብራዚልን በቴክኖሎጂ የታገዘ የምርጫ ስርዓት ለማጭበርርበር ምቹ ነው በማለት ስጋት መኖሩንም ጠቁመዋል።