ያለምዘርፍ በለንደን የማራቶን ውድድር አሸናፊ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዛሬው ዕለት መስከረም 22፣ 2015 ዓ.ም በለንደን በተካሄደው የሴቶች የማራቶን ውድድር ያለምዘርፍ የኋላው አሸናፊ ሆነች።
ያለምዘርፍ 32 ኪሎሜትር አካባቢ ወድቃ የነበረ ሲሆን ከዚያ አገግማም 2፡17፡26 በሆነ ሰዓት አስደናቂ ድል አስመዝግባለች።
በዚህ ውድድር ላይ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት መገርቱ አለሙ በሶስተኛነት አጠናቃለች። መገርቱ በ2፡18፡32 ሰዓት ውድድሩን በማጠናቀቅ ነው በለንደን ማራቶን የነሀስ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው።
በወንዶች የማራቶን ውድድር ኢትዮጵያዊው ልዑል ገብረ ስላሴ በጠንካራ ፉክክር ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።
ልዑል በኬንያዊው አሞስ ኪፕሩቶ ተበልጦ በ2፡05፡12 ውድድሩን በሁለተኛነት አጠናቋል። የቡድን አጋሮቹ ቀነኒሳ በቀለ አምስተኛ እና ብርሃኑ ለገሰ በስድስተኛነት ውድድሩን አጠናቀዋል። ያምናው የለንደን ማራቶን አሸናፊ ሲሳይ ለማ በሰባተኝነት ውድድሩን አጠናቋል።
የ23 ዓመቷ ያለምዘርፍ በውድድሩ መሃል የደረሰባትን ችግር ተቋቁማ ውድድሩንም ማሸነፍ የቻለች ሲሆን በዕድሜም ትንሿ ማራቶን አሸናፊ በመሆን ታሪክም ሰርታለች።
ያለምዘርፍ አሸናፊነቷ የተረጋገጠው በመጨረሻው 5 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ሲሆን በከፍተኛ ፍጥነትም በመስፈንጠር ከፍተኛ ግምት የተሰጣትን የአምናዋን የለንደን ማራቶን አሸናፊ ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይን አስከትላ ገብታለች። ያለምዘርፍ ከዚህ ቀደም ካስመዘገበችው ከፍተኛው ሁለተኛው የማራቶን ፈጣን ሰዓት ሶስት ሰኮንዶች ዘግይታ ነው የገባችው።
በከፍተኛ ደስታ ተውጣ የነበረችው ያለምዘርፍ “በለንደን ማራቶን በማሸነፌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለዚህ ውድድር ዝግጅት በጣም ጠንክሬ ሰርቻለሁ እናም ድሉን ማግኘቴ በጣም አስደናቂ ነው” ብላለች።
በማራቶን ታሪክ ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት እንዲሁም የአለም የ10 ኪሎሜትር ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነችው ያለምዘርፍ በሚያዝያ ወር በሃምቡርግ በነበረው ማራቶን በከፍተኛ ፍጥነት ውድድሩን በማጠናቀቅ በዓለም ታሪክ ፈጣን ሰዓት ካስመዘገቡ አትሌቶች በሰባተኛ ደረጃ እንድትቀመጥ አድርጓታል።












