የፍልስጤም ታጣቂዎች ኢየሩሳሌም ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች ተገደሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የፍልስጤም ታጣቂዎች ኢየሩሳሌም ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት ስድስት ሰዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች ስምንት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን የሕክምና ባለሙያዎች እና ፖሊስ ገለጹ።

የእስራኤል ፖሊስ እንዳለው "ሁለት ሽብርተኞች በመኪና መጥተው" በኢየሩሳሌም ሰሜናዊ ዳርቻ ላይ በሚገኝ ራሞት በተባለ መስቀለኛ መንገድ በሚገኝ የአውቶብስ ማቆሚያ ላይ ተኩስ በመክፈት ነው ጥቃት የፈጸሙት።

ከሥራ ውጪ የነበረ እና አንድ ሌላ ግለሰብ ጥቃት አድራሾቹ ላይ በከፈቱት የመልስ ተኩስ ታጣቂዎቹ መገደላቸውንም ፖሊስ ጨምሮ ገልጿል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን በጥቃቱ የተገደሉት በ25 እና በ79 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አምስት ወንዶች እና አንዲት የ60 ዓመት ሴት መሆናቸውን ዘግበዋል። የአካባቢው ሆስፒታል በጥቃቱ የቆሰሉ ሁለት ሰዎች በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ዘጠኝ ሰዎች እና በመስታወት ስብርባሪ ጉዳት የደረሰባቸው ሌሎች ሦስት ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

ለጥቃቱ ወዲያውኑ ኃላፊነት የወሰደ ታጣቂ ቡድን ባይኖርም፣ ሐማስ ኢየሩሳሌም ውስጥ የተፈጸመውን ጥቃት አወድሷል።

ፖሊስ እንዳለው በርካታ የፀጥታ አካላት ጥቃት የተፈጸመበትን አካባቢ የተቆጣጠሩ ሲሆን፣ ቦብም አስወጋጅ ክፍሎችም አካባቢው አስጊ አለመሆኑን አረጋግጠዋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ወታደሮች በአካባቢው መሰማራታቸውን እና ከፖሊስ ጋር በመተባበር ተጥርጣሪዎችን እየፈለጉ እንደሆነ ገልጿል።

"ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና የመከላከያውን ጥረት ለማጠናከር" ወታደሮች በእስራኤል በተያዘችው ዌስት ባንክ በምትገኘው ራማላህ ከተማ ዳርቻዎች የሚገኙ በርካታ ሥፍራዎችን መክበባቸውንም ጦሩ አክሏል።

የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ታጣቂዎቹ ጥቃቱ ከተፈፀመበት ራሞት አደባባይ በ10 ኪሎ ሜትር ገደማ ከሚርቁት ከአል ቁቤይባ እና ቋታና መንደሮች የወጡ እንደሆኑ ይታመናል።

የፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ሽሎሚ ባካር ጥቃቱ በተፈፀመበት ሥፍራ ሆነው ለቻነል 12 ቴሌቪዥን ሲናገሩ "የፖሊስ መኮንኖች እነዚህ ታጣቂዎች እንዴት ወደ ሥፍራው ሊመጡ እንደቻሉ እና ማን እንዳመጣቸው ለመረዳት እየሞከሩ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ በጥቃቱ የማን እጅ እንዳለበት እንደርስበታለን ብዬ አምናለሁ" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ጥቃቱን ተከትሎ ከፀጥታ ኃላፊዎች ጋር ሁኔታውን እየገመገሙ መሆናቸውን ጽሕፈት ቤታቸው አስታውቋል።

ሐማስ "በሁለት ፍልስጤማውያን ተዋጊዎች የተፈፀመ ልዩ ኦፕሬሽን እና ልዩ ተግባር " ያለውን ጥቃት አድንቋል።

ታጣቂ ቡድኑ "ይህ በሕዝባችን ላይ ለሚፈፀም የዘር ማጥፋት እና እስራኤል በኃይል በያዘችው ግዛት ለሚፈፀመው ወንጀል ተፈጥሯዊ ምላሽ ነው" ሲልም የጥቃቱን ተገቢነት ገልጿል።

የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሃን ዋድፑል " በሽብር ጥቃቱ እጅግ መደንገጣቸውን እና ሃሳባቸው ከተጎጂ ቤተሰቦች ጋር መሆኑን" ገልጸዋል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው ከተቃረበው እስራኤል በጋዛ ላይ ከምታካሂደው ወታደራዊ ዘመቻ ጋር በተያያዘ በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክም ተቃውሞ ገጥሟታል።