ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናሳ ወደ ጨረቃ የሚያደርገው የሮኬት ማስወንጨፊያ ሙከራ ለሁለተኛ ጊዜ ተቋረጠ
የናሳ አዲሱ የአርቴሚስ 1 ሮኬት ወደ ጨረቃ የሚያደርገውን ማስወንጨፊያ ሙከራ ለሁለተኛ ጊዜ መቋረጡ የመዘግየት ዕድል ገጥሞታል።
ባለሙያዎች ቅዳሜ ዕለት የስፔስ ማስጀመሪያ ሲስተም (ኤስ ኤል ኤስ) እንዲነሳ ለማድረግ በድጋሚ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። በነዳጅ መፍሰስ ምክንያት ሳይሳከ መቅረቱ ታውቋል።
መሐንዲሶች ሮኬቱን ለመፈተሽ ያሰቡ ሲሆን ጥገናው ከማስወንጨፊያው ይልቅ በዎርክሾፕ ውስጥ ሊሆን ይችላል ተብሏል።
አጠቃላይ ሂደቱ ለብዙ ሳምንታት መጓተት እንደሚያመራ እርግጥ ሆኗል።
በዚህም ከጥቅምት አጋማሽ በፊት ሦስተኛ ዙር የማስወንጨፊያ ሙከራ ላናይ እንችላለን ማለት ነው።
ኤስ ኤል ኤስ በዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኤጀንሲ ከተሠሩ እጅግ በጣም ጉልበተኛ ሮኬቶች አንዱ ነው።
ከ50 ዓመታት በኋላ የጠፈር ተመራማሪዎችን እና መሣሪያዎቻቸውን ወደ ጨረቃ ለመላክ የተሠራም ነው።
አብዛኛው ግዙፍ ግፊት ወደ ሦስት ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ፈሳሽ ሃይድሮጂን እና ኦክሲጅን ከስር ባሉት አራት ትላልቅ ሞተሮች ውስጥ በማቃጠል ይመጣል።
ቅዳሜ ማለዳ ላይ ባለሙያዎች የሮኬቱን ሃይድሮጂን ታንክ ለመሙላት ትዕዛዝ ሲልኩ የማንቂያ መልዕክቱ መፍሰስ እንዳለ አሳይቷል። በተደረገው ፍለጋም ችግሩ ሃይድሮጂን ወደ ተሽከርካሪው በሚያስተላልፈው ስፍራ መሆኑ ታውቋል።
ተቆጣጣሪዎች ሥራውን እንደገና ለማስጀመር በርካታ ጥገናዎችን ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። የአርቴሚስ 1 ተልዕኮ ባይሳካም የናሳ የአርቴሚስ ተልዕኮ ሥራ አስኪያጅ ማይክ ሳራፊን እንደተናገሩት የሮኬቱ ዕጣ ፈንታ በሰው የህዋ ጉዞ ላይ ተጽእኖ ስለሚኖረው በሥራው ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል።
"ይህ የማይታመን ከባድ ሥራ ነው። ይህ የዚህ ሮኬት የመጀመሪያ የሙከራ በረራ ነው። እንደተባለውም ዝግጁ ስንሆን እናስወነጭፋለን። በዚህ የመጀመሪያ ሙከራ ስለመሣሪያው እንማራለን። ተሽከርካሪውን እንዴት መጠቀም እንዳለብን እየተማርን ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የናሳ አስተዳዳሪ ቢል ኔልሰን “ይህን እንደ ስፔስ ፕሮግራማችን አንድ አካል ነው የምመለከተው ሲሆን የደህንነት ጉዳይ ደግሞ ቀዳሚ ነው” ሲሉ በሃሳቡ ተስማምተዋል።
በኤስ ኤል ኤስ ላይ ያለው ችግር በማስወንጨፊያው ላይ ሊስተካከል ይችላል። ነገር ግን ሮኬቱን ከጥቅም ውጭ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ባትሪዎች በድጋሚ ማረጋገጫ ስለሚያስፈልጋቸው ዎርክሾፕ መመለሱን አስፈላጊ አድርጎታል።
ሮኬቱን ወደ ኢንጂነሪንግ ክፍል መመለሱ ከጥቅምት አጋማሽ በፊት ሦስተኛውን የማስወንጨፍ ሙከራ እንደማይሳካ ያረጋግጣል።
የናሳ ተባባሪ አስተዳዳሪ የሆኑት ጂም ፍሪ በበኩላቸው “ባትሪ ለመፈተሽ ወይም ባትሪዎቹን ለመቀየር ወደ ኋላ መመለስ አለብን" ብለዋል። 100 ሜትር የሚረዝመው ሮኬት አላማው ኦሪዮን የተባለውን ካፕሱል ወደ ጨረቃ ለማድረስ የተሠራ ነው።
ይህም የአፖሎ ፕሮጀክት እአአ በ1972 ካበቃ በኋላ የተፈጠረ ነው። ናሳ መጀመሪያ ሰኞ ዕለት ነበር ሮኬቱን ለማስወንጨፍ የሞከረው። ተቆጣጣሪዎች አራቱ ትላልቅ ሞተሮች በትክክለኛ የሥራ ሙቀት ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ በመሆኑ እንዲቋረጥ ተደረገ።
በሚያሳዝን ሁኔታ መረጃ የሚያቀብለው መሣሪያ የተሳሳተ መረጃ እንደሚያስተላለፍ ታወቀ። መረጃው ተሳሳተ እንጂ ሮኬቱ ለመወንጨፍ ዝግጁ ነበር።