ጁሊያን አሳንጅ ከአሜሪካ ጋር በተደረሰ ስምምነት ከእስር ተፈታ

ታትሟል

ለዓመታት ከዘለቀ የሕግ ውዝግብ በኋላ የዊኪሊክስ መስራቹ ጁሊያን አሳንጅ ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ከዩናይትድኪንግደም እስር ቤት መለቀቁን ድርጅቱ አስታወቀ።

አሜሪካ ተላልፎ እንዲሰጣት እየጠየቀችው የነበረው አሳንጅ የተከሰሰበትን ወንጀል አምኖም በተደረሰ ስምምነት ነጻ ተብሏል።

የ52 ዓመቱ አሳንጅ የአገሪቱን የመከላከያ መረጃዎችን ለማግኘት እና ይፋ በማድረግ በማሴር ተከሶ ነበር።

ስለ ኢራቅ እና አፍጋኒስታን ጦርነቶች መረጃን ይፋ ያደረጉት የዊኪሊክስ ፋይሎች የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ስትል አሜሪካ ለዓመታት ስትከራከር ቆይታለች።

አሳንጅ ያለፉትን አምስት ዓመታት ለአሜሪካ ተላልፎ እንዳይሰጥ ሲከራከር በቆየበት በብሪታንያ እስር ቤት ውስጥ አሳልፏል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር የሆነው ሲቢኤስ እንደዘገበው ከሆነ በእንግሊዝ በእስር ላይ ያሳለፋቸው ዓመታት ከግምት ስለሚገቡ አሳንጅ በአሜሪካ የእስር ጊዜ አይጠብቀውም።

ከአሜሪካ ፍትህ ቢሮ በተላከ ደብዳቤ መሰረት አሳንጅ ወደ አውስትራሊያ ይመለሳል።

አሳንጅ ከአንድ ሺህ 901 ቀናት በኋላ እስር በኋላ ከአነስተኛዋ የቤልማርሽ እስር ቤት መውጣቱን ዊኪሊክስ በኤክስ ላይ አስፍሯል።

ከዚያም ወደ አውስትራሊያ ለመመለስ “ወደ ስታንስተድ አውሮፕላን ማረፊያ ተወስዶ ዩናይትድ ኪንግደምን ለቋል።”

ዊኪሊክስ በበይነ መረብ ያጋራው ቪዲዮ ላይ አሳንጅ ጂንስ እና ሰማያዊ ሸሚዝ ለብሶ ስታንስተድ የሚጠብቀው አውሮፕላን ከመሳፈሩ በፊት በመኪና ሲጓዝ ታይተል>

ቢቢሲ ይህንን ቪዲዮ ማረጋገጥ አልቻለም።

ባለቤቱ ስቴላ አሳንጅ “ይህ እውን እንዲሆን ለዓመታት ሲንቀሳቀሱ ለነበሩት ደጋፊዎቹ በሙሉ ምስጋና አቀርባለሁ” ስትል ኤክስ ላይ ጽፋለች።

በስምምነቱ መሠረት ከቀረቡበት ክሶች በአንዱ ጥፋተኛ መሆኑን በሰሜናዊ ማሪያና ደሴቶች ፍርድ ቤት ረቡዕ ዕለት ቀርቦ በማመን ጉዳዩ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ደሴቶቹ ከአሜሪካ ግዛቶች ይልቅ ለአውስትራሊያ የበለጠ ቅርብ ናቸው።

የአውስትራሊያ መንግሥት ቃለ አቀባይን ጠቅሶ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ ጉዳዩ “ከሚጠበቀው በላይ ተጓቷል” ብለዋል።

ጠበቃው ሪቻርድ ሚለር በሲቢኤስ ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም። ቢቢሲም መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገውን ጠበቃውን ለማነጋገር ሞክሯል።

አሳንጅ እና ጠበቆቹ የተመሰረቱበት ክሶች ፖለቲካዊ ናቸው ሲሉ ቆይተዋል።

በሚያዝያ ወር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአሳንጅ ላይ የቀረበውን ክስ እንዲቋረጥ ከአውስትራሊያ የቀረበላቸውን ጥያቄ እያጤኑት መሆኑን ተናግረው ነበር።

በቀጣዩ ወር ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም ፍርድ ቤት ለአሜሪካ ተላልፎ መሰጠቱን በመቃወም ይግባኝ መጠየቅ እንደሚችል ወስኖለታል።

የባይደን አስተዳደር “ከዚህ አሳፋሪ ክስ ራሱን ማራቅ አለበት” ስትል ባለቤቱ ከፍርዱ በኋላ ለጋዜጠኞች እና ለደጋፊዎቹ ተናግራለች።

የአሜሪካ አቃብያነ ህግ የዊኪሊክስ መስራች ላይ በ18 ክሶች በአብዛኛው ከስለላ እና በአፍጋኒስታን እና ኢራቅ ውስጥ ካሉ ጦርነቶች ጋር በተያያዘ የአሜሪካን ሚስጥራዊ ወታደራዊ መዝገቦችን እና ዲፕሎማሲያዊ መልዕክቶችን በማውጣት ክስ እንዲመሰረትበት ፈልገው ነበር።

እአአ በ2006 አሳንጄ የመሰረተው ዊክሊክስ "በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸሙት ሚስጥራዊ መረጃዎች መካከል ትልቅ ከሚባሉት አንዱ" ሲል የገለጸውን ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰነዶችን ማውጣቱን የአሜሪካ መንግስት ተናግሯል።

ድረ ገጹ እአአ በ 2010 በባግዳድ ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከአስር በላይ የሚሆኑ ሲቪል ኢራቃውያን ሲገደሉ የሚያሳይና ከአሜሪካ ወታደራዊ ሄሊኮፕተር የተቀረጸ ቪዲዮ ይፋ አድርጓል።

አሳንጅ ስዊድን ውስጥ በመድፈር እና በጾታዊ ጥቃት ሌላ ክስ ቀርቦበት የነበረ ቢሆንም ክሱን ክዷል።

የስዊድን ክስ ወደ አሜሪካ ተላልፌ እንድሰጥ ያደርገኛል በማለት ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ውስጥ ተደብቆ ሰባት አመታትን አሳልፏል።

የስዊድን ባለስልጣናት እአአ በ 2019 ክሱን ያቋረጡ ሲሆን በኋላም የእንግሊዝ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር አዋሉት።

ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የህግ ውዝግብ ውስጥ አሳንጄ በአደባባይ ብዙም አይታይም ነበር። ለዓመታት በጤና እጦት ሲሰቃይ እንደቆየ ሚነገር ሲሆን በ2021 በእስር ቤት ሆኖ አነስተኛ የደም መፍሰስ (ስትሮክ) እንፈደገጠመው ተነግሯል።