በአውስትራሊያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሳዎች በሙቀት ማዕበል ምክንያት ሞቱ

ታትሟል

በአውስትራሊያ በአንድ ግዛት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዓሳዎች በወንዝ ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ተገለጸ።

መጠነ ሰፊው የዓሳዎች ሞት የተዘገበው ትናንት አርብ ጥዋት በኒው ሳውዝ ዌልስ በምትገኘው መኒንዲ ከተማ ነው።

የግዛቲቱ አስተዳር በዳርሊንግ ባካ ወንዝ አሳዎች እየሞቱ ያሉበት ምክንያት በሙቀት ማዕበል መሆኑን ገልጿል።

ከሶስት ዓመታት በፊት እንዲሁ በርካታ ዓሳዎች ሞተው መገኘታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የኒው ሳውዝ ዌልስ የመጀመሪያ ደረጃ ኢንዱስትሪዎች ዲፓርትመንት በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው የሙቀት ማዕበሉ “ካጋጠመው የጎርፍ መጥለቅለቅ ጋር ተደምሮ ሁኔታዎችን አስከፊ አድርጓቸዋል” ብሏል።

በዓለም ላይ እየተከሰቱ ያሉ የሙቀት ማዕበሎች በጣም ተደጋጋሚ ፣ አስከፊ፣ ጠንካራና ረዘም ያሉ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ይህም በሰው ልጅ ምክንያት ከመጡ የአየር ንብረት ለውጦች ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

የኢንዱስትሪው ዘመን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አለም በአንድ ዲግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ የሞቀች ሲሆን የዓለም መንግሥታት የካርበን ልቀት መጠን ለመቀነስ ጥረት ካላደረጉ የሙቀት መጠንም ከዚህ በበለጠ ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

የመኒንዲ ነዋሪ የሆኑት ግሬም ማክክራብ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአሳዎቹን አሟሟት “እውነት የማይመስል፣ በህልም ላይ ያለን ነው የሚመስለው" ሲሉ ገልፀውታል።

የሞቱትና የበሰበሱት ዓሳዎች ከውኃው ውስጥ ብዙ ኦክስጅን ስለሚመጡም ተጨማሪ ዓሳዎች እንደሚሞቱ እየተጠበቀ ስለመሆኑም አስጠንቅቀዋልል።

የዳርሊንግ ባካ ወንዝ የአውስትራሊያ ትልቅ ወንዝ የሆነው የሙሬይ ዳርሊንግ ተፋሰስ ገባር ነው።

የዓሳዎቹ ሞት ለአካካቢው ማህበረሰብ አስጨናቂ ሁኔታ መፍጠሩንም ባለስልጣናቱ እንዲሁም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“በማዕድ ቤታችን ውስጥ አንድ አሳ ውጭ ላይ ሆኖ ሲበሰብስ የሚፈጠረውን ሁኔታ መገመት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሳዎች የከተማችን ወንዝ ሞልተውታል” ብለዋል።

በመኒንዲ ያለው የሙቀት መጠን ዛሬ ወደ 41 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ዳርሊንግ ባካ ወንዝን ለውሃ አቅርቦት እንደሚጠቀሙበት የተገለጸ ሲሆን “"የወንዙን ውሃ ለማጠብ፣ለመታጠብ እንጠቀምበታለን። ነዋሪዎች የወንዙን ውሃ እንደገና ለእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች መጠቀም አይችሉም" በማለት ግሬም ተናግረዋል።