ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዓለ ሲመታቸውን እንዲታደሙ በትራምፕ የተጋበዙት የቻይናው ፕሬዚዳንት ላይገኙ ይችላሉ ተባለ
በጥር ወር በሚደረገው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ላይ እንዲታደሙ በትራምፕ መጋበዛቸው የተነገረው የቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ የመገኘት እድላቸው አናሳ ነው ተባለ።
ለፕሬዚዳንቱ በዓለ ሲመት ዝግጅት ቅርበት ያላቸው ሁለት ምንጮች የቻይናው ፕሬዚዳንት መጋበዛቸውን ገልጸው፤ ነገር ግን ይታደማሉ ተብሎ አይጠበቅም ብለዋል።
በአሜሪካ የቻይና አምባሳደር በበዓለ ሲመቱ ይገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሌሎች የቻይና ባለስልጣናት ሊታደሙ እንደሚችሉ እኚሁ ምንጮች ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
መዛግብቶች እንደሚያሳዩት በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ በዓለ ሲመት ላይ የትኞቹም የውጭ መሪዎች ተገኝተው አያውቁም። የቻይናው ፕሬዚዳንት እንዲታደሙ መጋበዝ ያልተለመደ መሆኑን ሲቢኤስ ዘግቧል።
"ይህ ፕሬዚዳንት ትራምፕ አጋሮቻቸውን ብቻ ሳይሆን ጠላት እና ተፎካካሪዎች ከሆኑ አገራት መሪዎች ጋር ግልጽ ውይይት ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት ማሳያ ነው" ሲሉ የትራምፕ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም በነበሩ ንግግሮቻቸው ፕሬዚዳንት ሺን ሲያወድሱ ቢሰሙም ቻይና ላይ በተደጋጋሚ የሰላ ትችት ያቀርባሉ።
በሚቀጥለው ወር ላይ ስልጣን በሚረከቡበት ወቅት ከቻይና በሚመጡ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሬ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።
በጥቅምት ወር ላይ ትራምፕ ስለ ቻይናው መሪ "1.4 ቢሊዮን ሰዎችን ሰጥ ለጥ አድርጎ የሚገዛ ነው። ወደድንም ጠላንም ጎበዝ ሰው ነው" ሲሉ ጆ ሮጋን ለተባለ ጋዜጠኛ ተናግረው ነበር።
ትራምፕ በኃላፊነት የመረጧቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እጩ ማርኮ ሩቢዮ እንዲሁም የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ዋልትዝን ጨምሮ በርካቶች የቻይና መንግሥትን በከፍተኛ ሁኔታ ሲተቹ ይሰማሉ።
የቻይና መንግሥት በማርኮ ሩቢዮ ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2020 ደግሞ ወደ አገሩ እንዳይገባ ክልከላ ጥሎበታል።
የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ዋልትዝ አሜሪካ "ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ያለባትን ከፍተኛ ስጋት ለመቋቋም" በዩክሬን እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ጦርነቶችን ልታስቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአሜሪካ የስለላ ኤጀንሲዎች ስምንት ግዙፍ የአሜሪካ የቴሌኮሙኒኬሽን ኩባንያዎችን ከመጥለፉ ጀርባ ቻይና እንዳለችበት በቅርቡ አስታውቀው ነበር። እነዚህ መረጃ መንታፊዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያንን መረጃ አግኝተው ሊሆን እንደሚችል ዋይት ሃውስ ገልጿል።
ባለፈው ወር ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን በድጋሜ ያሸነፉት ትራምፕ ከካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ ከአርጀንቲና ፕሬዝዳንት ጃቪየር ሚሌይ እንዲሁም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጨምሮ ከበርካታ የውጭ ሀገራት መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።
እንደ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መዛግብት ከሆነ ከአውሮፓውያኑ 1874 ጀምሮ ዲፕሎማቶች እና አምባሳደሮች በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ቃለ መሃላ ላይ መገኘታቸው የተለመደ ቢሆንም የውጭ ሀገር መሪ በዓለ ሲመቱን ታድሞ አያውቅም።
በዚህ በዓለ ሲመት ላይ ሌሎች የውጭ አገራት መሪዎች እንዲታደሙ መጋበዛቸውን የተናገሩት የትራምፕ ቃል አቀባይ እነማን እንደሆኑ ዝርዝራቸውን አልገለጹም።