ለሆስፒታል መብራት ሲቀጥል የነበረው ሱዳናዊ የምኅንድስና ተማሪ ኤሌክትሪክ ይዞት ሞተ

የ27 ዓመቱ ሙሐመዲን ፋዱል ኢድሪስ ዋዲ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK/ALA DANEDN

የምስሉ መግለጫ, የ27 ዓመቱ ሙሐመዲን ፋዱል ኢድሪስ ዋዲ
ታትሟል

የውጊያ ቀጠና በሆነችው ዳርፉር ለሚገኝ ሆስፒታል መብራት ሲቀጥል የነበረ የምኅንድስና ተማሪ ኤሌክትሪክ ይዞት ሕይወቱ አለፈ።

የ27 ዓመቱ ሙሐመዲን ፋዱል ኢድሪስ ዋዲ ባለፈው ሐሙስ ፋሻር ከተማ ለሚገኘው ሳይድ አል-ሸሐዳ የተባለ የጤና ተቋም መብራት ለመቀጠል ሲሞክር ነው የሞተው።

በተባባሰው ውጊያ እና በተስፋፋው ዝርፊያ ሳቢያ ለመሥራት የተቸገረውን ሆስፒታል ለመጠገን ከተሰባሰቡ በጎ ፈቃደኞች አንዱ ነበር።

ጓደኞቹ አላ ዳንደን በሚል ቅጽል ስሙ የሚጠሩት ተማሪውን አንድ ወዳጁ ሲገልጸው “የሚታወቀው በፈገግታው ነበር። በጦርነቱም ጊዜ ሳይቀር” ብሏል።

በፋሻር ዩኒቨርስቲ አብሮት የተማረው አሕመድ ኢሳቅ “ለፋሻር ሕዝብ በሕይወቱ ዋጋ ከፍሏል” ብሏል።

ያለመታከት ለማኅበረሰቡ ይሰጥ በነበረው አገልግሎት እንደሚታወስም ተናግሯል።

በፌስቡክ ገጹ ላይ ከፎቶው ጋር ተያይዞ የተቀመጠው ጽሑፍ “ዕድል አጠገባችን እስክትመጣ አንጠብቅ። ዕድልን እኛው እንፍጠራት” ይላል።

በሱዳን ውጊያው ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወጣት በጎ ፈቃደኞች ‘የአል-ታውራ ወጣቶች’ በሚል በፋሻር ለሕክምና ሰጭዎች ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሳውዝ ሆስፒታል ከተባለው ሆስፒታል ውጭ በሰሜናዊው የደቡብ ዳርፉር ያሉ ሆስፒታሎች በውጊያው ምክንያት ሥራ አቋርጠዋል።

አከባቢው የውጊያ ቀጠና በመሆኑ ሐኪሞች ወደ ሆስፒታል መሄድ አልቻሉም።

“በመጀመሪያው ሳምንት በሳውዝ ሆስፒታል ጉዳት የደረሰባቸውን ተቀብሎ እርዳታ ለመስጠት ሲሞክር ነበር። እንደ ንብ ታታሪ ሠራተኛ ከመሆኑም በተጨማሪ በቀና ንግግሩ ሥነ ልቦናችን ጠንካራ እንዲሆን ያግዘን ነበር” ሲል ነው አሕመድ ጓደኛውን የሚገልጸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ ሠራተኞች ሊገቡበት ያልቻሉትን ሆስፒታል ለመጠገን ሞክረዋል። ሆስፒታሉ ዝርፊያም ደርሶበት ነበር።

ከከተማው በቅርብ ርቀት በሚገኙት አቡ ሻንባት እና ዛም ዛም ወታደራዊ ካምፖች የሚሄዱ ቁስለኞችን ሆስፒታሉ መርዳት እንዲችል በድጋሚ መክፈት ነበር ዕቅዳቸው።

በዚህ አካባቢ ከ20 ዓመታት በፊት በዳርፉር ብሔር ተኮር ጥቃት የደረሰባቸው ማኅበረሰቦችም ይኖራሉ።

ምኅንስድና ተማሪው ሙሐመዲን እና ጓደኞቹ ለሆስፒታሉ ጥገና፣ ምግብ ለመግዛትና የሕክምና ቁሳቁሶች ለመሸመት ገንዘብ እያሰባሰቡ ነበር።

“ከፋርማሲዎች ጋር ተነጋግሮ መድኃኒት በማግኘት ረገድ ጎበዝ ነበር” ይላል ጓደኛው።

ሕልሙ ሆስፒታሉ በድጋሚ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ማድረግ ነበር።

25 በጎ ፈቃደኛ የሕክምና ባለሙያዎች እና 80 ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞች ተሰባስበው ሆስፒታሉን ባለፈው ሳምንት መልሰው መክፈት ችለዋል።

ሆኖም ግን አብዛኛው አካባቢ ከኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቆራርጧል።

የምኅንድስና ተማሪው ያለፈው ሐሙስ የሆስፒታሉን የተቆረጠ መብራት ለመቀጠል እየሞከረ ሳለ ነው የተጎዳው።

መጀመሪያ ላይ ራሱን እንደሳተና ኋላ ላይ ወደ ሳውዝ ሆስፒታል እንደተወሰደ ጓደኛው ይናገራል።

ከ48 ሰዓታት በኋላ በሆስፒታሉ ያሉ በጎ ፈቃደኞች ሊያተርፉት ስላልቻሉ ሕይወቱ ቅዳሜ ምሽት አለፈ።

“ጦርነቱ ካበቃ በኋላ በከተማው ማዕከል እንደምንገናኝ ቃል ገብተን ነበር። የጥይትን ድምጽ በሙዚቃ እንደምንተካ ነበር ተስፋችን። ሙዚቃ እና ደስታ ይወድ ነበር። ግን አላ ዳንደን ትቶን ሄዷል። ለሱ ስንል የሕዝቡን ሕይወት ለማሻሻል የምናደርገውን ጥረት እንቀጥላለን” ብሏል ጓደኛው።

ጦርነቱ አገሪቱን እንዳልነበረች አድርጓታል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ሲገደሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መዲናዋ ካርቱምን ጨምሮ ቁልፍ ቦታዎችን ለመቆጣጠር መዋጋት ቀጥለዋል።

ሁለቱን ወገኖች ወደ ውይይት ጠረጴዛ የማምጣትና ተኩስ የማስቆም ጥረቶች እንደቀጠሉ ናቸው።

መሠረታዊ አገልግሎት ማግኘት ከባድ በሆነባት ካርቱም ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት አልቻሉም።

ሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች ለአጭር ጊዜ የተኩስ አቁም አድርገው በሳዑዲ አረቢያ፣ ጅዳ እንደሚነጋገሩ የሳዑዲ ባለሥልጣኖች ቢገልጹም፣ ከዚህ ቀደም የተደረጉ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ጦርነቱን መግታት አልቻሉም።