ከባለሥልጣን ቤት ንብረት የዘረፈችው የቤት ሠራተኛ ጠንቋይ ቤት ተያዘች

ታትሟል

ከአንድ ባለሥልጣን ቤት ንብረት ዘርፋ የተሰወረችው ኬንያዊት የቤት ሠራተኛ ጠንቋይ ቤት በቁጥጥር ሥር ዋለች።

የኬንያ ፖሊስ እንዳለው በስርቆት ተጠርጥራ በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሴት “ታዋቂ ከሆነው” ጠንቋይ ቤት የተገኘችው “ከእስር የሚያስመልጣት” መተት ለማግኘት ነው።

ሚሪያም ሙዌሉ የተባለችው ይህች የቤት ሠራተኛ በስም ካልተጠቀሰው የኬንያ መንግሥት ባለሥልጣን ቤት ጥሬ ገንዘብ እና ውድ ጌጣ ጌጦችን የሰረቀችው ከሦስት ሳምንት በፊት ነበር።

መርማሪ ፖሊስ ሴቲቱ በጠንቋዩ ቤት በወፍ ደም ውስጥ ተነክራ ሳለ በስርቆት ወንጀሉ ከተባበራት ግብረ አበሯ ጋር በቁጥጥር ሥር አውያታለሁ ብሏል።

ፖሊስ ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲሞክር፣ በእድሜ የገፉት ጠንቋይ የፖሊስ አባላቶቹ ለማሸሽ ይረዳል ያሉትን የመተት ቃላት ቢደረድሩም፤ ሕግ አስከባሪዎች ግን ተልዕኳቸውን ከመወጣት አላገዳቸውም ብሏል በመግለጫው።

በዚህ ወቅት ተጠርጣሪዋም የጠንቋዩ ቃላት ፖሊሶቹን ያስወግዳል ብላ በማመን ዐይኖቿን ጨፍና ነበር ሲል የኬንያ ወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ገልጿል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን ተጠርጣሪዋን፣ ግብረ አበሯን፣ የተዘረፈውን ጥሬ ገንዘብ፣ ውድ ጌጣ ጌጦች እንዲሁም ጠንቋዩ ይጠቀሙባቸው የነበሩ ቁሳቁሶችን ምስል ይፋ አድርጓል።

ተጠርጣሪዋ ግምቱ ከ33 ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ የሚያወጣውን ንብረት ከዘረፈች በኋላ ለሦስት ሳምንታት ተሰውራ ነበር ተብሏል።

የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት በሕግ የሚፈለጉ ሰዎች ጥንቆላ ከሕግ ተጠያቂነት ስለማያስመልጣቸው ጊዜያቸውን እንዳያባክኑ አሳስቧል።