ትራምፕ ብራዚል ላይ 50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ በመዛት የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ክስ እንዲቋረጥ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg/Getty
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከደቡብ አሜሪካዋ አገር ጋር የገቡበትን እሰጣ ገባ በሚያባብስ ሁኔታ በብራዚል በተመረቱ ሸቀጦች ላይ የ50 በመቶ ቀረጥ ለመጣል ማቀዳቸውን ገለጹ።
ትራምፕ ይህንን እቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት በማኅበራዊ ሚዲያ በተሰራጨው በሰሞነኛው የታሪፍ ደብዳቤ ነው።
ፕሬዝዳንቱ በዚህ ደብዳቤ፤ ብራዚልን በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ላይ "ጥቃት" በመሰንዘር እና በቀድሞው ቀኝ አክራሪ ፕሬዝዳንት ዣየር ቦልሶናሮ ላይ "የሀሰት ውንጀላ ምርመራ" በማካሄድ ከስሰዋል።
ቦልሶናሮ፤ በ2022 የተካሄደውን የአገሪቱ ምርጫ ውጤት በመገልበጥ ሴራ በነበራቸው በተባለው ሚና ምክንያት ክስ ላይ ናቸው።
የብራዚል ፕሬዚዳንት ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በብራዚል ላይ የሚደረገው የግብር ጭማሪ የአጸፋ ምላሽ እንደሚያስከትል የገለጹ ሲሆን በአገሪቱ የፍትህ ስርዓት ላይም ማንኛውም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንዳይደረግ አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የቦልሶናሮን የፍርድ ሂደት በተመለከተ ከሉላ ጋር እንካ ስላንቲያ ውስጥ ገብተዋል።
ሉላ በወቅቱ፤ ብራዚል ከማንም የሚመጣን "ጣልቃ ገብነት" እንደማትቀበል" እና "ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ" ተናግረዋል።
ረቡዕ ዕለት ደግሞ ትራምፕ፤ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ ያደረጉት የመዳብ አስመጪዎች ላይ የተጣለ የ50 በመቶ ቀረጥ ከሐምሌ 25/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ይህ ውሳኔው የተላለፈው ከብሔራዊ ደህንነት ስጋት አንጻር መሆኑን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።
ትራምፕ በዚህ ሳምንት እንደ ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና ስሪ ላንካ ያሉ የንግድ አጋሮቻቸውን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ላሉ 22 አገራት በላኳቸው ደብዳቤዎች፤ ከሐምሌ 25 ጀምሮ ከአገራቱ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ የሚጣሉ አዳዲስ ታሪፎችን ዘርዝረዋል።
እነዚህ እርምጃዎች ፕሬዝዳንቱ ሚያዝያ ላይ ካቀረቧቸው በኋላ በፋይናንስ ገበያው ላይ በተፈጠረው ውድቀት ምክንያት ለጊዜው በይደር እንዲቆዩ ያደረጓቸውን ውሳኔዎች በድጋሚ ወደ ተግባራዊነት የመለሱ ናቸው።
ወደ ብራዚል የተላከው ደብዳቤ ግን አገሪቱን በግዝፉ ዒላማ ያደረገ እና ዋይት ሐውስ ከዚህ ቀደም ከብራዚል በሚገኙ ሸቀጦች ላይ ጥሎት በነበረው የ10 በመቶ ታሪፍ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንደሚደረግ የሚያስጠነቅቅ ነው።
ከበርካታ ሌሎች አገሮች በተለየ መልኩ አሜሪካ ባለፈው ዓመት ከብራዚል ካስገባችው ሸቀጥ የበለጠ ምርት ወደ አገሪቱ ልካለች።
ትራምፕ በደብዳቤያቸው፤ ሊጣል የታቀደውን 50 በመቶው የታሪፍ መጠን "የአሁኑን አገዛዝ ከባድ ኢፍትሀዊነት ለማስተካከል... አስፈላጊ" መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ መስሪያ ቤት በብራዚል ዲጂታል የንግድ ልምዶች ላይ '301' የተባለውን ምርመራ እንዲጀምር ትዕዛዝ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
ይህ ዓይነቱ እርምጃ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ቀረጥ ለመጣል ስትጠቀምበት ወደ ነበረው መሰረት ያለው የሕግ አካሄድ ፊቷን ማዞሯን የሚያመለክት ሲሆን የታሪፉ ተግባራዊነት ስጋትንም ያጠናክረዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ወቅት ብራዚል የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን ዒላማ ያደረገ ግብርን ለመጣል ስታቅድ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።
ትራምፕ በደብዳቤው የብራዚል መንግሥት፤ "በነፃ ምርጫዎች እና በአሜሪካውያን መሠረታዊ የመናገር ነጻነት ላይ ስውር ጥቃቶች" እንደሰነዘረች እንዲሁም "የአሜሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን" ላይ ሳንሱር እንደፈጸመች በመጥቀስ ከስሰዋል።
የማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቶች ላይ የተጣሉ የእግድ ትዕዛዞችን በተመለከተ በብራዚል ፍርድ ቤት የተላለፉ ውሳኔዎችን እየተሟገቱ ካሉ የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ትራምፕ ባለቤት የሆኑበት የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ትራምፕ ሚዲያ ነው።
በተጨማሪም አገሪቱ የ2022ቱን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን አስመልክቶ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ አካውንቶችን ለማገድ ፈቃደኛ አለመሆኑን ተከትሎ፤ ትዊተር በመባል ይታወቅ የነበረውን የኤለን መስክን 'ኤክስ' ለጊዜው አግዳ ነበር።
ባለፈው ወር የብራዚል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የማኅበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች በመድረኮቻቸው ላይ ለተለጠፈው ይዘት ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ ወስኗል።
ትራምፕ በዚህ ደብዳቤ የቀድሞውን የብራዚል ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮን "በእጅጉ አብረዋለሁ" በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል። በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ እየተካሄደ ያለውን የፍርድ ሂደት "ዓለም አቀፍ ውርደት" በማለት ጠርተውታል።
ትራምፕ እና ቦልሶናሮ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ወዳጅነት የነበራቸው ሲሆን በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በ2019 በዋይት ሐውስ ተገናኝተዋል። ቦልሶናሮም "የትሮፒኩ ትራምፕ" በሚል ቅጽል ስም ይጠሩ ነበር።
ሁለቱም፤ በምርጫ የተሸነፉ ሲሆን ሽንፈታቸውን በይፋ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም።
ከ2019 እስከ 2022 ብራዚልን የመሩት ቦልሶናሮ፤ ሉላ ምርጫውን ካሸነፉ በኋላ በጥር 2023 በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው አሰማርቶ የመንግሥት ሕንጻዎች በመውረር መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ ሙከራ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ቦልሶናሮ በወቅቱ አሜሪካ ውስጥ የነበሩ ሲሆን ከሁከት ፈጻሚዎቹ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ወይም በሴራው ውስጥ ምንም ዓይነት ተሳትፎ እንደሌላቸው በመግለጽ ክሱን አስተባብለዋል።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ትራምፕ፤ ቦልሶናሮ ላይ የቀረበውን ክስ እርሳቸው ላይም ከቀረበው ውንጀላ ጋር አነጻጽረዋል።
"ይህ በፖለቲካ ተቀናቃኝ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት እንጂ ሌላ አይደለም፤ በብዙ የማውቀው ነገር ነው!" ሲሉ ተደምጠዋል። ቦልሶናሮ በምላሹ ትራምፕ ላደረጉላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ እሁድ ዕለት በማደግ ላይ ያሉ አገራትን በብራዚል ያሰባሰበው የብሪክስ ጉባኤ ነቃፊ ናቸው። ትራምፕ፤ ብራዚል ጭምር የምትገኝበትንቡድን "ፀረ-አሜሪካዊ" በማለት የጠሩ ሲሆን እነዚህ ሀገሮች ተጨማሪ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደጣልባቸው ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ሉላ በማኅበራዊ ሚዲያ ለተላለፈው የትራምፕ ዛቻ ሰኞ ዕለት ምላሽ ሰጥተዋል። ሉላ፤ "ዓለም እንደተለወጠ ማወቅ አለበት" ብለዋል። "ንጉሠ ነገሥት አንፈልግም" ሲሉም አክለዋል።















