የትራምፕ አስተዳደር አዳዲሶቹን ቻይና ሠራሽ 'ሂውማኖይድ' ሮቦቶች አገደ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የትራምፕ አስተዳደር ማክሰኞ ዕለት በአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት ላይ "ተቀባይነት የሌላቸው አደጋዎች" ያስከትላሉ በሚል በውጭ አገር የተመረቱ እና ወደ አሜሪካ የሚገቡ አዳዲስ ሮቦቶችን ማገዱን አስታወቀ።

ይህ እርምጃ የሚመለከተው ሂውማኖይድ ሮቦቶችን እና ባለአራት እግር ማሽኖች ነው። ብዙዎቹ የሚመረቱት ከአሜሪካ ጋር በሮቦቲክስ እና ሰው ሠራሽ አስተውሎት ከፍተኛ ፉክክር እያደረገች በምትገኘው ቻይና ነው።

የፌደራል ኮሙኒኬሽን ኮሚሽን (ኤፍሲሲ) በዳታ ማዕከላት እና በሶላር ፓኔል ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ ኃይል መቀየሪያዎችን (power inverters) ማስመጣት በአሜሪካ ምጣኔ ሃብት ላይ አደጋ ይደቅናል በሚል አግዷል።

በዋሺንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቤይጂንግ አሜሪካ የንግድ ጉዳዮችን "ፖለቲካዊ" ማድረግ እና "ውሃ በማይቋጥሩ ምክንያቶች" እገዳ መጣልን ስትቃወም ቆይታለች ብሏል።

የኤፍሲሲ ሊቀመንበር ብሬንዳን ካር እንዳሉት ኤጀንሲው "የአሜሪካን ወሳኝ የአቅርቦት ሰንሰለት ለማስጠበቅ" የበኩሉን እያደረገ ነው።

ኤፍሲሲ ሂውማኖይድ ሮቦቶችን የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የእቃዎች እና አገልግሎቶች ዝርዝር ውስጥ አካትቷቸዋል።

እገዳው የሚመለከተው አዳዲስ በውጭ አገር የሚመረቱ የላቁ የሮቦት መሣሪያዎችን እና የኃይል መቀየሪያዎችን ሲሆን ቀደም ሲል በኤፍሲሲ ፈቃድ የተሰጣቸውን ማንኛውንም ነባር ሞዴሎች መሸጥ ወይም ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን አያግድም።

ኤፍሲሲ በውጭ አገር የሚመረቱ የኃይል መቀየሪያዎችን መጠቀም፣ የውጭ አገር ኩባንያዎች በቀላሉ እንዲያጠፏቸው፣ ዳታቸው እንዲሰረቅ፣ በርቀት እንዲቆጣጠሯቸው እና ስለላ እንዲያካሂዱ እንዲሁም "በውጭ መንግሥት ተዋናዮች ወይም በሌላ መልኩ በሳይበር ጥቃት እንዲጋለጡ ያስችላቸዋል" የሚል ስጋትን ዘርዝሯል።

ከአሜሪካ ውጭ የተሰሩ ሮቦቶችን መጠቀም "ድብቅ ዓላማ ያላቸው ቡድኖች አሜሪካውያንን እንዲከታተሉ፣ የውጭ የስለላ አገልግሎቶችን አቅም እንዲያሻሽሉ ወይም ሮቦቶቹን በርቀት እንዲያዝዙ" ያስችላል ሲል አክሏል።

በዋሽንግተን የሚገኘው የቻይና ኤምባሲ ቤጂንግ ፍላጎቷን በሚጻረሩ ላይ "ሁሉንም አስፈላጊ እርምጃዎች እንደምትወስድ" ገልጾ፣ ሁሉም አገሮች "ለአዎንታዊ እና ለበጎ ተግባር" የሰው ሠራሽ አስተውሎት አቅምን ለማዳበር አብረው እንዲሠሩ አሳስቧል።

አሜሪካ "የራሷን የበላይነት ለማሳየት የምትከተለውን መንገድ፣ የቻይና ኩባንያዎችን ማጥላላቷን እና ማዕቀብ እንደሚጣልባቸው ማስፈራራትን እንድታቆም" ጥሪ አቅርቧል።

ቢቢሲ ዋና ዋና የቻይና ሮቦት አምራቾች የሆኑትን ዩኒትሪ፣ ዩቢቴክ እና አጊቦትን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

የትራምፕ አስተዳደር የዓለማችን ሁለተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላት ቻይና ጋር ያለውን የንግድ አለመመጣጠን ለመፍታት በሚሞክርበት በዚህ ወቅት የቻይና ኤክስፖርት በአሜሪካ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገበት ነው።

ቻይና በዓለም ላይ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ወደ ውጭ የምትልክ ዋነኛ አገር ብትሆንም፣ በከፍተኛ ታሪፍ ምክንያት ከአሜሪካ ገበያ ውጭ ሆናለች።

ዋሽንግተንም የአገርን ደህንነት ለመጠበቅ፣ የቤጂንግን ወታደራዊ ዘመናዊነት ለማዘግየት እና አሜሪካ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘርፍ ያላትን መሪነት ለማስቀጠል በሚል ዘመናዊ የአሜሪካ ሴሚኮንዳክተሮችን ለቻይና እንዳይሸጡ አግዳለች።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስኮት ቤሴንት የቻይና የአይቲ ኩባንያዎች የአሜሪካን የአዕምሯዊ ንብረት ሰርቀዋል በሚል ክስ ማዕቀብ ሊጣልባቸው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል ።

የቻይና መንግሥት በምላሹም የአገሪቷ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥራ "በራሱ ቁርጠኝነት፣ ጥረት እንዲሁም በዓለም አቀፍ ትብብር ውጤት" እንደሆነ ተናግሯል።

የቻይና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፋብሪካዎች እና ቤቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሂውማኖይድ ሮቦቶችን በፍጥነት እያመረቱ ነው።