ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በግብፅ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስደተኛ "እስር ቤት ከገባ ከአራት ቀናት በኋላ" ሕይወቱ ማለፉን ምንጮች ተናገሩ
በግብፅ ዋና ከተማ ካይሮ ይኖር የነበረ አንድ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ወደ እስር ቤት ከገባ ከአራት ቀናት በኋላ ሕይወቱ ባለፉት ለግለሰቡ ቅርብ የሆኑ ሦስት ምንጮች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ያሬድ ገረመው የተባለው ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ያለፈው "ድካም ይዞት ነው" የሚል መረጃ ቢወጣም፤ ምንጮች ግን በግለሰቡ አሟሟት ላይ ጥያቄዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል።
የአምስት ዓመት ልጅ አባት የሆነው ያሬድ ሕይወቱ እንዳለፈ የተሰማው ረቡዕ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም. እንደሆነ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ምንጮች ተናግረዋል።
ምንጮቹ እንደሚያስረዱት፣ ያሬድ ካይሮ ከተማ ወደሚገኝ እስር ቤት የገባው ከመሞቱ አራት ቀናት በፊት ቅዳሜ ሐምሌ 11 ነበር። ኢትዮጵያዊው ስደተኛ የታሰረው ከመኖሪያ ፈቃድ ጋር በተያያዘ እንደነበር አንድ ምንጭ ጠቅሰዋል።
ምንጩ ሲያስረዱ "በቀን 11 ጠዋት ወደ ሥራው ሲሄድ ነው የተያዘው። ከእዚያ በኋላ ሰኞ ፍርድ ቤት አቀረቡት" ብለዋል። ይህንን የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቶ ከእስር እንደሚለቀቅ ተገልጾ እንደነበር ምንጩ ተናግረዋል።
ሌላ ምንጭ በበኩላቸው ሊጠይቁት ወደ እስር ቤት በሄዱበት ወቅት "የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ተቀብያለሁ፣ ዛሬ ማታ እወጣለሁ" ብሏቸው እንደነበር አስታውሰዋል። "ከእዚያ በኋላ ይመለሳል ብዬ ስጠብቅ በማግስቱ ደግሞ ሞቱን ተረዳሁ" ብለዋል።
ምንጮቹ እንደሚገልጹት፣ የእስር ቤት ኃላፊዎች ያሬድ ሕይወቱ ያለፈው "ታሞ ሆስፒታል ከገባ በኋላ" እንደሆነ ተናግረዋል። ሕይወቱ ያለፈውም ባጋጠመው "ድካም" ምክንያት እንደሆነ መግለጻቸውንም አንስተዋል።
በካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የአስከሬን ምርመራ እንዲያደርግ ጥያቄ ማቅረቡን የሚናገሩት ምንጮች ግን ይህንን አይቀበሉትም። አንድ ምንጭ፣ የያሬድ ሕይወት ያለፈበት መንገድ የተለየ ነው የሚል ጥርጣሬያቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊው በሞተበት ምሽት "ገንዘብ እንዲከፍል ተጠይቆ" እንደነበር ይናገራሉ። "ከእስር ቤት አውጥተው ብር ሲጠይቁት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ኤሌክትሪክ ጠፋ። መብራት ጠፍቶ ሲመለስ ልጁ መሬት ወድቆ ነው የተገኘው። ተመትቶ ነው" ሲሉም ያገኙትን መረጃ አጣቅሰው ተናግረዋል።
ሌሎች ሁለት ምንጮችም ይህንን ጥርጣሬ እንደሚጋሩት ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ በግል የአስከሬን ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል አቅም እንደሌላቸው አንስተዋል።
ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማሳወቃቸውንም ጠቅሰዋል።
ቢቢሲ የያሬድን ሞት በተመለከተ በግብፅ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ተቋም ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።
ግብፅ ውስጥ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የማኅበረሰብ አመራሮች፤ እስር እና ማዋከብ እንደሚደርስባቸው በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያውያኑ ማኅበረሰብ አመራር የሆኑ አንድ ምንጭ ኢትዮጵያውን ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ "ወረቀት ቢኖራቸውም በፖሊስ ይታሰራሉ" በማለት ይከስሳሉ።
"እስር ቤት ውስት ብዙ ታሳሪ ስላለ መቀመጫ ቦታ የለም፣ የሚተኙበት ቦታ የለም፤ [ማድረግ የሚችሉት] መቆም ነው። መቀጥት ከፈለግክ ብር ትከፍላለህ" በማለትም ሁኔታውን ይገልጻሉ።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ግብፅ ውስጥ ያለውን የስደተኞች ሁኔታ በተመለከተ በሰኔ መጨረሻ በወጣው ሪፖርት፤ ፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች "ለወራት የሚቆይ የዘፈቀደ ዘመቻ፣ ሕገ ወጥ እስር እና ከአገር መባረር" እየደረሰባቸው እንደሆነ ገልጾ ነበር።
የሂውማን ራይትስ ዎች ሪፖርት እንደሚያመለክተው ይህ ዓይነቱ እንግልት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይም ደርሷል። የደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኤርትራ ስተደኞችም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳጋጠማቸው ተገልጿል።