በዩክሬን ጥቃት ሳቢያ በሩስያ ቁልፍ የሆነ ድልድይ ፈረሰ

የፎቶው ባለመብት, Telegram
ዩክሬን ባደረሰችው ጥቃት ለሩስያ ጉልህ ጠቀሜታ ያለው ድልድይ ተሰበረ።
ዩክሬን በሩስያ ኩርስክ ግዛት የከፈተችውን ወረራ ቀጥላ ሴይም በተባለው ወንዝ ላይ የነበረውን ድልድይ አፍርሳለች።
የሩስያ ባለሥልጣን እንዳሉት ዩክሬን ግሉሽኮቮ ከተማ አካባቢ በምታደርገው ዘመቻ በአካባቢው መቆራረጥ ተከስቷል።
የፈረሰው ድልድይ ሩስያ ለወታደሮች ግብዓት የምታቀርብበት ነው። መፍረሱም ክፍተት ሊፈጥርባት ይችላል።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የዩክሬን ወታደሮች በኩርስክ ግዛት ይዞታቸውን እያጠናከሩ ነው ብለዋል።
በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሏቸው የሩስያ ይዞታዎችን ለሩስያ የሚመልሱት ሩስያ የዩክሬን ይዞታዎችን ስትመልስ መሆኑን አክለዋል።
ዩክሬን የሩስያን ድንበር ጥሳ ጥቃት ከከፈተች ሁለተኛ ሳምንት ሆኗል። በዩክሬን ጥቃት ከ120 ሺህ በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
“ዩክሬን የሩስያን ግዛት የመያዝ ፍላጎት የላትም” ሲሉ የዘለንስኪ ዋና አማካሪ ሚካሄሎ ፖዶሊክ ተናግረዋል።
“በኩርስክ ግዛት በወታደራዊ መንገድ ሩስያ ወደ ፍትሐዊ ድርድር እንድትመጣ ማድረግ ነው የምንፈልገው” ብለዋል።
የዩክሬን መከላከያ ኃላፊ ኦልክሳንደር ሲርስኪ እንዳሉት የዩክሬን ጥቃት ቀጥሏል።
“ወታደሮቻችን መዋጋት ይቀጥላሉ። ወደ ጠላቶቻቸን ሦስት ኪሎሜትር ተጠግተዋል” ብለዋል።
ከድንበር 13 ኪሎሜትር ከሚርቀው ማላ ሎክኒያ መንደር “ብዙ እስረኞች” ለመውሰድ እንዳቀዱ ገልጸዋል።
ዩክሬን ወደ ሩስያ ዘልቃ መግባቷን ስትቀጥል የሩስያ ቤልጎርድ ግዛት አመራሮች አምስት መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እንዲወጡ አሳስበዋል።
የቤልጎርድ ግዛት አገረ ገዢ ቫያ ቸስላቭ ግላድኮቭ “ከነሐሴ 19 ጀምሮ አምስት መንደሮችን እንዘጋለን። ነዋሪዎች ንብረታቸውን እንዲያወጡና እነሱም እንዲወጡ እናግዛቸዋለን” ሲሉ በቴሌግራም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዩክሬን ወታደሮች በሩስያ ድንበር በምዕራብ በኩል መግፋት ሲቀጥሉ የሩስያ ወታደሮች ደግሞ በዩክሬን ምሥራቅ በኩል እየገፉ ነው።
የሩስያ ወታደሮች ሰሪክቫ የተባለ የዩክሬን ከተማ ሰኞ ዕለት መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ይህም የሩስያን ወታደሮች ወደ ፖክሮስክ ከተማ እንዲቃረቡ ያደርጋቸዋል።
አካባቢው በዩክሬን ምሥራቃዊ ግንባር በኩል ለወታደሮች ግብዓት የሚቀርብበት ዋነኛ ቀጠና ነው።
ፖክሮስክ የሚገኘው በሩስያ ቁጥጥር ሥር ካለው ዶንተስክ ግዛት በሰሜን ምዕራብ ነው።
የከተማው አስተዳዳሪ ሰርጌ ዶብሪያክ፣ የሩስያ ወታደሮች እየተቃረቡ በመምጣታቸው ነዋሪዎች እንዲወጡ አሳስበዋል።
የሩስያ ወታደሮች በመገበያያ ማዕከል ላይ ጥቃት ሰንዝረው ሰባት ሰዎች መጎዳታቸው ተገልጿል።
ዶንተስክን እንዲመሩ ሩስያ የሾመቻቸው ዴኒስ ፑሽሊን እንዳሉት በከተማው ጥቃት እየደረሰ ነው።
ሮይተርስ እንደዘገበው፣ ባለፉት 24 ሰዓታት ሦስት ንጹኃን ዜጎች ሲገደሉ አምስት ሰዎች ቆስለዋል።
ሩስያ በ2014 በግዛቷ የጠቀለላችት ክሬሚያ ውስጥ የሚገኝና በፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የተሠራ ድልድይ ላይ የተቃጣ ሚሳዔል እንደከሸፈ ተገልጿል።
ከርች በሚባለው በዚህ ድልድይ ላይ ጥቃት ለማድረስ ዩክሬን በተደጋጋሚ ጥረት አድርጋለች።












