ሾርባ ውስጥ የሸኑ ቻይናዊያን ታዳጊዎች 300 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

ሾርባ ውስጥ ሽንታቸውን የሸኑ ሁለት ቻይናዊያን ታዳጊዎች 2.3 ሚሊዮን ዩዋን አሊያም 300 ሺህ ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው።

ባለፈው የካቲት በቻይናው ግዙፍ የሾርባ ሬስቶራንት ሀይዲላዎ ገብተው ይህን ድርጊት የፈፀሙት ታዳጊዎች ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል።

ዕድሜያቸው 17 የሆነው ሁለቱ ታዳጊዎች በስካር መንፈስ የፈፀሙትን ድርጊት በቪድዮ ቀርፀው በማሕበራዊ ሚድያ አጋርተዋል።

በሸንት የተበከለውን ሾርባ ሰዎች እንዳልጠጡት ቢነገርም ሀይዲላዎ የተባለው ግዙፍ ምግብ ቤት ከድርጊቱ በኋላ ለተስተናገዱ በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞቹ ክፍያ ለመፈፀም ቃል ገብቷል።

መጋቢት ላይ ሬስቶራንቱ ደንበኞችን ለመካስ ያደረገውን ከግምት አስገብቶ ለደረሰበት ኪሳራ 23 ሚሊዮን ዩዋን እንዲከፈለው ጠይቋል።

ባለፈው አርብ የሻንግሀይ ፍርድ ቤት ታዳጊዎች የሬስቶራንቱን መብት ጥሰዋል እንዲሁም ስሙን አጉድፈዋል ሲል ፈርዷል። አክሎ ታዳጊዎቹ የኩሽና ዕቃዎችን መርዘዋል በዚህም "በሕዝቡ ዘንድ ድንጋጤ ፈጥረዋል" ብሏል።

ፍርድ ቤቱ የታዳጊዎቹ ቤተሰቦች "በሥነ-ሥርዓት የማሳደግ ግዴታቸውን አልተወጡም" በማለት ካሳውን እንዲከፍሉ መወሰኑን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

2 ሚሊዮን ዩዋን ለደረሰው ኪሳራ እንዲከፈል፤ 130 ሺህ ዩዋን ደግሞ የኩሽና ዕቃዎች ላይ ለደረሰው ኪሳራ እና ለፅዳት፤ በተጨማሪ 70 ሺህ ዩዋን ለክስ ሒደት ወጭ መሸፈኛ እንዲሆን ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቷል።

ነገር ግን ሀይዲላዎ ደንበኞች ሊከፍሉ ከሚገባቸው በላይ ገንዘብ ካሳ ለመክፈል መወሰኑ "በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ" ታዳጊዎቹ ይህን ወጪ መሸፈን አይገባቸውም ብሏል።

ምግብ ቤቱ በአውሮፓውያኑ ከየካቲት 24 እስከ መጋቢት 8 ለተጠቀሙ ከ4 ሺህ በላይ ደንበኞቹ ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍንና 10 እጥፍ ካሳ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል።

አክሎም የሾርባ ማብሰያ ዕቃዎችን ሙሉ በሙሉ በአዲስ መተካቱን፤ የፅዳት እና የፀረ-ተህዋስ ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል።

በሲቹዋን ግዛት በጂያንያንግ ከተማ የመጀመሪያውን ምግብ ከፍቶ በመላው ቻይና በፍጥነት የተስፋፋው ሀይዲላዎ በተለያዩ ሀገራት ከ1 ሺህ በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

ምግብ ቤቱ ለደንበኞቹ በሚሰጠው ላቅ ያለ አገልግሎት እና ቤተሰባዊ በሆነ መስተንግዶው ይታወቃል።