ሩሲያ የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሊቀመንበርነትን መያዟ ጥያቄ አስነሳ

የጸጥታው ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ሩሲያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የሊቀመንበርነትን ሥፍራ መያዟ ጥያቄ አስነሳ።

ዩክሬን ይህንን በመቃወምም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ውድቅ እንዲያደርጉት ጥያቄ አቅርባለች።

አስራ አምስት አባላትን በያዘው የጸጥታው ምክር ቤት የሊቀመንበርነቱን ሥፍራ አገራቱ በመቀያየር የሚረከቡት ሲሆን የመሪነቱም ሥፍራ ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ይሆናል።

ለመጨረሻ ጊዜ ሩሲያ የፕሬዚደንትነቱን ሥልጣን በተረከበችበት በአውሮፓውያኑ የካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟ ይታወሳል።

ይህም ማለት የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንቷ በጦር ወንጀል በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ በተጣለባቸው አገር እየተመራ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ተቋም ያልሆነው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በፕሬዚዳንት ፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው።

ዩክሬን ቅሬታዋን ብታቀርብም የምክር ቤቱ ቋሚ አባል የሆነችው አሜሪካ ሩሲያን የሊቀመንበርነቱን ሥፍራ ከመውሰድ እንደማታግድ አስታውቃለች።

ከአሜሪካ በተጨማሪ ሌሎች የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ቻይና ናቸው።

የሊቀ መንበርነቱ ሥፍራ ይህንን ያህል ሚና ባይኖረውም በተባበሩት መንግሥታት የሩሲያ አምባሳደር ቫሲሊ ኔቤንዚያ፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ለማየት እቅድ እንዳላቸው ለአገሪቱ የዜና ወኪል ታስ ተናግረዋል።

ወጥ የሆነውን የዓለም ሥርዓትም ለመተካት አማራጭ አዲሱን የዓለም ሥርዓት መዘርጋትንም በተመለከተ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ሩሲያ የፕሬዚዳንትነት ሥፍራን መቆናጠጧ “የሚያስከፋ ቀልድ ነው" ሲሉ የገለጹት ሲሆን “በዓለም አቀፍ ደረጃ የጸጥታ መዋቅር አሰራርም ላይ ችግር መሆኑን የሚያሳይ ነው” ሲሉም አሳሳቢነቱን አስረድተዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ ሚካሂሎ ፖዶሊያክ በበኩላቸው፣ እርምጃው “የዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ነው። ወረራ ያካሄደች አገር፣ የሰብዓዊና የወንጀል ሕግ ደንቦችን የምትጥስ ፣ የተባበሩት መንግሥታት ሰነድን የማታከብር፣ የኒውክሊዬር ስጋቶችን ችላ የምትል አገር የዓለም ቁልፍ የደኅንነት ተቋምን መምራት አትችልም “ ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ባለፈው አመት የጸጥታው ምክር ቤት አሰራሩን እንዲያሻሻል ወይም "ሙሉ በሙሉ እንዲበተን" ጥሪ አቅርበዋል። ለዚህም ምክንያታቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለፈጸመችው በረራ በቂ እርምጃ አልወሰደም የሚል ሲሆን ሩሲያም ከአባልነቷ እንድትታገድ ጠይቀዋል።