የናይጄሪያዋ ግዛት በረመዳን ጾም ወቅት በአደባባይ የሚመገቡ ሰዎችን በእስር እቀጣለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የናይጄሪያዋ ካኖ ግዛት በረመዳን ወር በጾም ወቅት በአደበባይ መመገብን ጨምሮ ሃይማኖታዊ ደንቦችን የጣሱ እስር እንደሚጠብቃቸው አስጠነቀቀች።
ይህንንም የሚቆጣጠረው ግዛቷ ያቋቋመችው እስላማዊ ፖሊሶች ናቸው።
ሂስባህ ቦርድ በመባል የሚታወቀው ሃይማኖታዊው የፖሊስ ሃይል ትናንት ሃሙስ በሰጠው መግለጫ በቅዱሱ የረመዳን ወር የማህበረሰቡን እሴት ተላልፈው ጥፋት የሚፈጽሙ ሰዎች እንደሚቀጡ ማስጠንቀቁን የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
“በጾም ወቅት በአደበባይ የሚመገቡ ታዳጊዎችም ቢሆኑ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” ሲሉ የቦርዱ ዋና አዛዥ ሃሩን ኢብኑ ሲና ተናግረዋል
ሐሙስ እለት የተጀመረውንም የጾም ወቅት ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዲከናወን ቦርዱ ፖሊሶችን ወደ መስጊዶች ማሰማራቱንም አዛዡ አክለው ተናግረዋል።
የካኖ ግዛት በአብዛኛው የእስልምና ተከታዮች ያሉባት ሲሆን እስላሚ ህግንም ትከተላለለች።
ይህንንም በበላይነት የሚያስከብረው ሂስባህ ቦርድ የተባለው ነው።
በዓለም ላይ ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች ዓመታዊውን የረመዳን ጾም በያዝነው ሳምንት ሐሙስ ጀምረዋል።
በጾም ወቅት አማኞች ከንጋት እስከ ምሽት ራሳቸውን ከምግብ እና ከመጠጥ ያርቃሉ።
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ እንደ ቅዱስ ወር በምትታየው ረመዳን ይቅር ባይነት፣ በጎ አድራጎት የሚታይበት እንዲሁም መንፈሳዊነት የሚጎለብትበት ነው።
በዚህች ወርም ከፍተኛ የእስልምና እምነት ተከታዮች ባሏቸው አገራት የከተሞች እንቅስቃሴ ይቀዘቅዛል።
አንዳንድ አገራት በረመዳን ወቅት ቱሪስቶችን መቀበል የሚያቆሙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የተለየ ህግን ያወጣሉ።
በሞሮኮ በረመዳን ፆም ወቅት የእስልምና እምነት ባይከተሉም በአደባባይ ሲበሉና ሲጠጡ ከተያዙ እስከ ስድስት ወራት እስራት ያስቀጣል። ይህም በህገ መንግሥቱ የተካተተ ሲሆን ባለፈው ዓመትም አምስት ሰዎች በአደባባይ ሲበሉና ሲጠጡ ተይዘው ተቀጥተዋል።
ሞሮኮ ብቻ ሳይሆን በተለይም በባህረ ሰላጤው ውስጥ በርከት ያሉ የአረብ እና የሙስሊም ሀገራት ተመሳሳይ ህግጋት አላቸው።
ሳዑዲ አረቢያ ከዚህ አለፍ ባለ በአደባባይ ሲበላና ሲጠጣ የተገኘ ሙስሊም ያልሆነን ሰው ከሀገር አባርራለሁ የሚል አዋጅ ማውጣቷ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።












