ውጥረት የበዛበትን የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ለማርገብ ብሊንከን ቤይጂንግ ገቡ

አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ንግግር ለማድረግ ቤይጂንግ ገቡ።

ይህ የብሊንከን ጉዞ የአሜሪካ ዲፕሎማት ወደ ቻይና ሲጓዝ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ያደርገዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት የጉዞ አላማ እጅግ ውጥረት ያየለበትን የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ማረጋገት ነው ብለዋል።

ብሊንከን ይህን ጉዞ ለማድረግ አቅደው የነበረው ከአምስት ወራት በፊት የነበረ ቢሆንም ግዙፉ የቻይና ፊኛ አሜሪካ ሰማይ ላይ ከታየች በኋላ ጉዟቸውን መሰረዛቸው ይታወሳል።

ብሊንከን ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እአአ 2021 መጀመሪያ ላይ ስልጣን ከተረከቡ ወዲህ ቻይናን የጎበኙ ትልቁ የአሜሪካ ባለስልጣን ናቸው።

አሜሪካ ከብሊንከን ጉብኝት ትልቅ ውጤት እንደማትጠብቅ የገለጸች ሲሆን ይህ ጉብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ጉልህ የሆነ ለውጥ ላያመጣ እንደሚችል ሁለቱም አገራት ያምኑበታል።

አሜሪካ የጉብኝቱ አላማ ሁለቱ አገራት ወደፊት ለንግግር ከፍት እንዲሆኑ እና ሰላይ ናት የተባለችው የቻይና ፊኛ በአሜሪካ የአየር ክልል መገኘቷ የፈጠረውን ውጥረት ማርገብ ነው ትላለች።

በዚህ መካከል ቻይና የራሴ አንድ ግዛት አካል ነች በምትላት ታይዋን አቅራቢያ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች።

የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት ያላት፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች እና ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት ባለቤት ከሆነችው ታይዋን ጋር አሜሪካ የቅርብ ግንኙነት እንዳላት ይታወቃል።

ብሊንከን በቻይና ቆይታቸው ከቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኪን ጋንግ እንዲሁም ከአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከፍተኛ ኃላፊ ዋንግ ዪ ጋር ይገናኛሉ። ብሊንከን ከፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ ጋር ስለመገናኘታቸው የተባለ ነገር የለም።

ኅዳር ወር ላይ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዢ ጋር በባሊ ከተገናኙ በኋላ በሁለቱ ኃያላን አገራት መካከል ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ተሰግቶ የነበረውን ‘የቀዝቃዛ ጦርነት’ ስጋት አርግቧል።

ይሁን እንጂ የሰላይዋ ፊኛ መገኘት በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል ይፋዊ ግንኙነትን አቀዛቅዞ ቆይቷል።

በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት፣ የረቀቁ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ውጤቶች ንግድ አለመግባባት፣ በአሜሪካ የፌንታሊን እጽ መስፋፋት እንዲሁም የቻይና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከብሊንከን አጀንዳዎች መካከል ይገኙበታል።