የአውሮፓ አገራት ሩሲያ ጋዝ ልታቋርጥብን ትችላለች በሚል ፍጆታ ለመቀነስ ተስማሙ

ታትሟል

የአውሮፓ አባል አገራት ሩሲያ የጋዝ አቅርቦቷን ልታቋርጥ ትችላለች በሚል ስጋት የጋዝ ፍጆታቸውን በ15 በመቶ ለመቀነስ ተስማሙ።

አውሮፓውያኑ የጋዝ አቅርቦትን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመች ነው የሚሏት ሩሲያ፤ ባሻት ጊዜ ወደ አውሮፓ የምትልከውን የጋዝ መጠን ልትቀነስ ወይም ልታቋርጥ ትችላለች የሚል ስጋት አላቸው።

የአውሮፓ የኢነርጂ ሚንስትሮች ዛሬ ማክሰኞ ሐምሌ 19/2014 ዓ.ም. ውይይት ካደረጉ በኋላ የጋዝ ፍጆታቸውን ለመቀነስ ተስማምተዋል።

የአውሮፓ አገራት የ15 በመቶ የጋዝ ፍጆታቸውን ለመቀነስ የተስማሙት ከነሐሴ 2014 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 2015 ዓ.ም. ባሉት ወራት ነው።  

የአውሮፓ ኅብረት የጋዝ ፍጆት መቀነስ ያስፈለገው የኃይል አቅርቦትን እንደ ጦር መሳሪያ አድርጋ የምትጠቀመው ሩሲያ፤ የምትልከውን ጋዝ ልታቋርጥ ስለምትችል እና ከክረምት ወራት በፊት ጋዝ መቆጠብ ስላለብን ነው ብሏል።

የሩሲያ ግዙፉ ጋዝ አቅራቢ ኩባንያ ጋዝፕሮም፤ ወደ አንዳንድ የአውሮፓ አገራት ይልክ የነበረውን የጋዝ አቅርቦቱን አቋርጧል።

ጋዝፕሮም ቡልጋሪያ፣ ፊንላንድ፣ ኔዘርላንድስ እና ፖላንድ ለሚገዙት ጋዝ ክፍያቸውን በዶላር ወይም በዩሮ ሳይሆን በሩብል እንዲከፍሉ ተጠይቀው ፍቃደኛ ባለመሆናቸው አቅርቦቱ ተቋርጦባቸዋል ብሎ ነበር።

ሩሲያ በምዕራባውያን የተጣለባትን በርካታ ማዕቀቦችን ለመቋቋም ያስችላት ዘንድ ከወስደቻቸው እርምጃዎች መካከል መገበያየ ገንዘቧ ዋጋውን እንዳያጣ ማድረግ አንዱ ነው።

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት የጋዝ ፍጆታቸውን ለመቀነስ የተስማሙት በፍላጎት ሲሆን፤ የአቅርቦት መጠኑ ግን አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ከደረሰ ፍጆታ መቀነሱ አስገዳጅ ይሆናል።

በርካታ የአውሮፓ አገራት የኃይል ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት ከሩሲያ በሚያስገቡት ጋዝ ነው። ባለፈው ዓመት 40 በመቶ የአውሮፓን የጋዝ ፍላጎት ያሟላቸው ሞስኮ ነበረች።

ከሩሲያ ከፍተኛ ጋዝ ከሚገዙ አገራት መካከል ጀርመን፣ ጣሊያ፣ ኔዘርላንድስ እና ፈረንሳይ ተጠቃሽ ናቸው።

ጀርመን 80.4 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ጋዝ ከሩሲያ ታስገባለች። ጣሊያ 66.4 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲሁም ኔዘርላንድስ 59.8 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ከሩሲያ የሚገዙት የጋዝ መጠን ነው።