የአሜሪካ እና የደቡብ ኮሪያ ስምምነት አደገኛ መሆኑን ሰሜን ኮሪያ አስጠነቀቀች

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን እህት አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ በቅርቡ የደረሱት ስምምነት ወደ ከፋ አደጋ ሊያመራ እንደሚችል አስጠነቀቁ።

ተፅዕኖ ፈጣሪዋ ኪም ዮ ጆንግ፣ የሰሜን ኮሪያ የኑክሌር መከላከያ አቅም ፍፁም በሚባል ደረጃ የበለጠ አስተማማኝ መሆን አለበት ማለታቸውን የኮሪያ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።

አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ ኑክሌር የታጠቁ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦቿን ለማሰማራት እና ሴዑልን በኑክሌር ዕቅዷ ውስጥ ለማሳተፍ የተስማማች ሲሆን፣ ደቡብ ኮሪያም በምላሹ የራሷን የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች ማበልጸግ ለመተው ተስማምታለች።

“ዋሽንግተን ዲክላሬሽን” የተባለው ስምምነት በይፋ የተገለጸው በዚህ ሳምንት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከደቡብ ኮሪያ አቻቸው ዮን ሱክ ይሎ ጋር ዋሽንግተን ውስጥ በተወያዩበት ወቅት ነው።

ኪም ዮ ጆንግ ስምምነቱን ጠቅሰው “ጠላቶች የኑክሌር ጦር ልምምዶችን ለማድረግ በተዘጋጁ ቁጥር እና የኑክሌር መሣሪያዎችን በኮሪያ ሰርጥ ባሰማሩ ቁጥር፣ ከእነርሱ ጋር ተመጣጣኝ ለመሆን እራሳችንን የመከላከል መብታችን ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል” ብለዋል።

በመሆኑም ውሳኔው “የሰሜን ምሥራቅ እስያን ሰላም እና ደኅንነት እንዲሁም የዓለምን ደኅንነትን ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ ያደርጋል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት ኪም፣ በኮሪያ ሠራተኞች ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴው ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ሲሆን፣ በወንድማቸው ኪም ጆንግ ኡን ዘንድ ተደማጭነት እንዳላቸውም ተዘግቧል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ስምምነቱ በሰሜን ኮሪያ ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል የአጋሮችን ትብብር ያጠናክራል ሲሉ አድንቀውታል።

ፕሬዝዳንት ዩን በበኩላቸው ስምምነቱ የኑክሌር ጦር መሣሪያን በመጠቀም ጥቃትን ለመከላከል እና አጋሮችን ለመጠበቅ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የአሜሪካን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለውታል።

በሌላ በኩል ቻይና ባላንጣዎቹ አገራት “ሆነ ብሎ ውጥረቶችን ከማስነሳት፣ ግጭትን ከማነሳሳት እና ዛቻ ከመሰንዘር” እንዲቆጠቡ አሳስባለች።

ስምምነቱ አሜሪካ በአርባ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለደቡብ ኮሪያ ኒውክሌር የታጠቁ ሰርጓጅ መርከቦችን ከኑክሌር ቦንቦች እና ሌሎች መሣሪያዎች ጋር በመላክ ቁርጠኝነቷን በግልጽ እንድታሳይ የሚያስችል ነው።

ሁለቱ አገራት ዕቅዶች ላይ ለመነጋገርም የኑክሌር አማካሪ ቡድን ያቋቁማሉ።

በሴዑል የሚገኙ ፖለቲከኞች ዋሽንግተን በሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዴት እና መቼ መጠቀም እንዳለባት በማቀዱ በኩል የበለጠ እንድትሳተፍ ሲገፋፉ ቆይተዋል።

የሰሜን ኮሪያ ኑክሌር መሣሪያ በመጠንና በውስብስብነቱ እያደገ መምጣቱ ሴዑልን እና ዋሺንግተንን እያስጨነቀ መጥቷል።

ፒዮንግያንግ ደቡብ ኮሪያን ኢላማ ማድረግ የሚችል ታክቲካዊ የኑክሌር ጦር መሣሪያ እያበለጸገች ሲሆን፣ አሜሪካ መድረስ የሚችል ረጅም ርቀት ተወንጫፊ መሣሪያዋንም እያሻሻለች ነው።

በስምምነቱ መሠረት አሜሪካ ደቡብ ኮሪያን የመጠበቅ ግዴታ ያለባት ሲሆን፣ ቀደም ብሎም ደቡብ ኮሪያን ከጥቃት ለመከላከል፣ አስፈላጊ ከሆነ የኑክሌር ጦር መሣሪያ ልትጠቀም እንደምትችል ቃል ገብታለች።

ሆኖም በደቡብ ኮሪያ አንዳንዶች የአሜሪካ ቁርጠኝነት ላይ ጥርጣሬ እንደገባቸው እና አገሪቷ የእራሷ የኑክሌር ፕሮግራም ላይ እንድታተኩር ጥሪ አቅርበዋል።