አሜሪካ ባሕር ሰርጓጅ የኒኩለር መሣሪያ ተሸካሚ መርከቦችን ወደ ደቡብ ኮሪያ ልታሰማራ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ አዲስ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራረሙ።
ሁለቱ አገራት በዚህ ስምምነታቸው እያደገ የመጣውን የሰሜን ኮሪያ ጠብ አጫሪነት ለመቋቋም የሚያስችሉ ትብብሮችን ለማድረግ ተስማምተዋል።
አሜሪካ ወደ ደቡብ ኮሪያ ባሕር ሰርጓጅ ኒኩለር ተሸካሚ መርከብ ለማሰማራት ቃል የገባች ሲሆን ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ራሷን ችላ የኒኩለር ጦር መሣሪያን የማበልጸግ ነገር እርግፍ አድርጋ ለመተው ተስማምታለች።
ሁለቱ አገራት ከዚህ ቀደምም ቢሆን ጠንካራ ወታደራዊ የትብብር ስምምነት ያላቸው ሲሆን አሜሪካ በማንኛውም ሁኔታ ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት ከደቡብ ኮሪያ ጎን በመሰለፍ ከለላ እንድትሰጥ ስምምነት አላቸው።
አሜሪካ አሁን ይህን ባሕር ሰርጓጅ መርከብ ወደ ደቡብ ኮሪያ የምታሰማራው በተደጋጋሚና በተለያየ ጊዜ ነው።
አዲሱ የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት ዩን አገራቸው በአሜሪካ ከለላና ጥበቃ ብቻ ተማምና ቁጭ ማለት እንደሌለባትና የራሷን ኒኩለር ማበልጸግ እንደሚኖርባት በምርጫ ወቅት ሲቀሰቅሱ ነበር።
ሰሞኑን በዋሺንግተን ከአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን ከተገናኙ በኋላ አገራቸው ደቡብ ኮሪያ ኒኩለር ጦር መሣሪያ የማበልጸጉን ጉዳይ እንደማታነሳ ተስማምተዋል።
በምትኩ ግን አሜሪካ ከዚህ ወዲያ በሚኖራት የኒኩለር መሣሪያዎች እቅድ ውስጥ ከደቡብ ኮሪያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ስምምነት ተደርሷል።
ፒዮንግያንግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ ድረስ የሚያልሙ አህጉር አቋራጭ የሚሳኤል ሙከራዎችን ከማድረጓም በላይ ታክቲካል የኒኩለር መሳሪያዎችን እያበለጸገች ነው።
ይህ ሁኔታ ለሁለቱ በወታደራዊ ቃል ኪዳን ውስጥ ላሉት ዋሺንግተንና ሲዮል አሳሳቢ ሆኖባቸው ቆይቷል።
ከሰሜን ኮሪያ ሊሰነዘር የሚችልን ማንኛውንም ወታደራዊ ጥቃት ለመመከት ሁለቱ አገራት ዋሺንግተን ዲክሌሬሽን የሚባል የቆየ ስምምነት አላቸው።
በዚህ ስምምነት መሠረት አሜሪካ በማንኛውም ሁኔታ ደቡብ ኮሪያ ኒኩለር መሣሪያ ጭምር በመጠቀም ከሰሜን ኮሪያ ጥቃት ትከላከላታለች።
ዋሺንግተን በጉብኝት ላይ የሚገኙት የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዪኦል የአሜሪካንን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ይህ ለወራት ወስጥ ውስጡን ሲሰራበት የቆየ ነው የተባለው አዲሱ ወታደራዊ ስምምነት አሜሪካ ከ40 ዓመት በኋላ ባሕር ሰርጓጅ የኒኩለር መሣሪያ ተሸካሚ መርከቦችን ወደ ደቡብ ኮሪያ በማስጠጋት ቁርጠኝነቷን በግልጽ እንድታሳይ የሚያስችል ነው።
ከዚህም ሌላ ሁለቱ አገራት በጋራ የኒኩለር ምክክር ቡድን ይመሠርታሉ።
ደቡብ ኮሪያ ወዳጃቸው አሜሪካ በኒኩለር መሣሪያ አጠቃቀምና እቅድ ዙርያ ብዙም አታሳትፈንም በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ያቀርቡ ነበር።
የሰሜን ኮሪያ ኒክሊየር መሣሪያ በመጠንና በውስብስብነቱ እያደገ መምጣቱ ሶኦልንና ዋሺንግተንን እያስጨነቀ መጥቷል።
በተለይ ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ ኒኩለር መሣሪያ የምትጠቀመው ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ትንኮሳዋ ምን ላይ ሲደርስ ነው የሚለው ሁልጊዜም ያስጨንቃቸዋል።
ለዚህም ነው በወዳጅ አገር ከመተማመን የራሳችንን ኒኩለር ማበልጸግ አለብን ወደሚል ሐሳብ የገቡት።
አሜሪካ ይህን የኒኩለር ሐሳብ ለማስጣል የቃላት ሽንገላ ብቻ በቂ እንዳልሆነ በመረዳቷ ነው ወደ ተግባራዊ እርምጃ የገባችው ይላሉ ተንታኞች።












