በሕንድ እና ባንግላዲሽ በርካቶችን የገደለው ጎርፍ ሚሊዮኖችን መውጫ አሳጥቷል ተባለ

ታትሟል

በሕንድ እና ባንግላዲሽ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የመብረቅ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ቢያንስ 59 ሰዎች ሞቱ።

የአደጋ መከላከል ሠራተኞች መውጪያ ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመታደግ በርብርብ ላይ ናቸው።

የጎርፉ መጠን በመጪዎቹ ቀናት አሁን ካለው በላይ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የባንግላዲሽ መንግሥት አሁን ያለው ጎርፍ እንደ አውሮፓውያኑ ከ2004 ወዲህ እጅግ የከፋው ነው ሲል ገልጾታል።

ባለፈው ሳምንት የተከሰተው ከባድ ዝናብ የአገሪቱን ሰሜናዊ ምሥራቅ ተራራማ አከባቢዎችን አካሎ ጎረቤቷ ሕንድ ላይም ጉዳት አስከትሏል።

በአካባቢዎቹ ትምህርት በጊዜያዊ መጠለያዎች እንዲሰጥ እየተደረገ ሲሆን ጎርፉ ባስከተለው የውሃ ሙላት ግንኙነት የተቋረጡባቸው ነዋሪዎችን ለመታደግ ወታደሮች በስፍራው ተሰማርተዋል።

ኮምፓኒጋኒ በተባለው ስፍራ የሚኖር ግለሰብ “እስከ ባለፈው አርብ ጠዋት አካባቢው በሙሉ በውሃ ተጥልቅልቆ ነበር። ሁላችንም መውጫ አጥተን ተቸግረን ነበር” ሲል አስተያየቱን ለኤኤፍፒ ሰጥቷል።

“ቀኑን ሙሉ በቤታችን ጣሪያ ላይ ቆይተን ጎረቤቶቻችን በሠሩት ጊዜያዊ ጀልባ ከአደጋው ተርፈናል። እናቴ በሕይወቷ እንዲህ ዓይነት አደጋ አይታ እንደማታውቅ ነግራኛለች” ሲል አክሏል የ23 ዓመቱ አስተያየት ሰጪ።

ሌላ ከጎርፍ አደጋው የተረፈች ሴት ደግሞ ለሁለት ቀናት ምግብ መመገብ እንዳልቻለች ተናግራለች።  

“የውሃ ሙላቱ የተከሰተው በጣም በፍጥነት ነው። በዚህም ምክንያት ያለንን ነገር ይዘን መውጣት አልቻልንም። ሁሉ ነገራችንን ውሃ ውስጥ ሆነን እንዴት ማብሰል እንችላለን” ስትል አስተያየቷን ለዜና ወኪሉ ሰጥታለች።

በጎረቤቷ ሕንድ አሳም በተሰኘችው ግዛት 1.8 ሚሊዮን የሚሆን ሰው ለ5 ቀናት በጣለው ተከታታይ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተለያየ መንገድ ተጎጂ መሆናቸው ተሰምቷል።

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ሂማንታ ቢስዋ ሳርማ በጎርፉ ተይዘው ላሉ ነዋሪዎች አስፈላጊው እርዳታ እንዲቀርብ ማዘዛቸውን ለጋዜጠኖች ተናግረዋል።

ባንግላዲሽ በዚህ ሳምንት በዚህ አደጋ ከመጠቃቷ በፊት ሲለት የተባለችው ግዘቷ ላይ ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ የከፋ ነው የተባለውን አደጋ ባለፈው ወር አስተናግዳ ነበር።

በአደጋው ቢያንስ 10 ሰዎች ሲሞቱ 4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ተጎጂ ሆነዋል። ታዲያ አገሪቱ ከዚህ አደጋ ገና በማገገም ላይ ሳለች ነው የዚህ ሳምንት አደጋ የተከሰተው።

በባንግላዲሽ ሕግ አውጪ የነበረ ሰይድ ራፊኩል አገሪቱ ቀደም ብላ በሰብአዊ ቅውስ ውስጥ እንደነበረች ተናግሯል።

“ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የሲለት ግዛት ዙሪያ በውሃ ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ በሚለዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መውጫ አጥተው ነበር ” ሲል ለሮይተርስ አስተያየቱን ሰጥቷል።