ተጠባቂው ጨዋታ በማንቸስትር ዩናይትድ የበላይነት ተጠናቀቀ

ታትሟል

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ተጠባቂ ጨዋታ ትላንት ሰኞ ምሽት ተከናውኖ ማንቸስተር ዩናይትድ ሊቨርፑልን 2 ለ 1 ማሸነፍ ችሏል።

ማንቸስተር በጄደን ሳንቾ እና ማርከስ ራሽፎርድ አማካይነት ባስቆጠራቸው ጎሎች ቀዳሚ መሆን ችሏል። ግብፃዊው ሞሐመድ ሳላህ የሊቨርፑልን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል።

ሁለቱ ቡድኖች ሦስት ነጥብ ማግኘት ሳይችሉ ነው ትላንት የተገናኙት።

ሊቨርፑል በመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ከፉልሃም እና ክሪስታል ፓላስ ጋር አቻ ተለያይቷል።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ደግሞ በብሬንትፎርድ እና ብራይተን አስደንጋጭ ሽንፈት ተከናንቧል።

ውጤቱን ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ሊቨርፑል 16ኛ ደረጃን ለመያዝ ተገዷል።

የማንቸስተር ዩናይትድ ማንሰራራት

በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ ከደረሰባቸው ሽንፈት በተጨማሪ ማንቸስተር ዩናይትዶች ባለፈው ሳምንት በብሬንትፎርድ 4 ለ 0 መሸነፋቸው ያለቡትን ዝቅተኛ ደረጃ ያሳያል።

ደጋፊዎች ደግሞ በክለቡ ባለቤቶች ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ከጨዋታው በፊት ጀምረው ያሰሙ ነበር። ሜዳ ውስጥም ተቃውሞው ቀጥሎ ነበር።

ክለቡ አዲስ ያስፈረመው ብራዚላዊው አማካይ ካስሚሮ ከጨዋታው በፊት ከደጋፊዎች ጋር ተዋውቋል።

ባለፈው ዓመት በሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ሊቨርፑል 9 ለ 0 በሆነ ድምር ውጤት ለማሸነፍ ችሏል።

ሊቨርፑልን አጨዋወት ለመመከት ቴን ሃግ በፍጥነት መጫወትን መርጠዋል። ከመጀመሪያው ጎል በፊትም አንቶኒ ኤላንጋ ጎል ለማስቆጠር ከጫፍ ደርሶ የጎሉ ቋሚ ኳሱን መልሶበታል።

ተከላካዩ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ ከተገጣሚው ሞሐመድ ሳላህ ጋር ነበረው ፍልሚያ ቡድኑ የነበረውን መነሳሳት ያሳያል።

ጨዋታው ለቴን ሃግ ትልቅ ትርጉም ነበረው። አሰልጣኙ አምበላቸው ማጓየርን እና ኮከቡን ሮናልዶን በተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠው ጨዋታውን ጀምረዋል። ቢሸነፉ አሰልጣኙ በዚህ ውሳኔያቸው ትልቅ ውግዘት ይጠብቃቸው ነበር።

ድሉ ሌሎች ድንቅ ምሽቶች ለመጀመር ማብሰሪያ እንደሆነ ይታሰባል።

ቴን ሃግ ከጨዋታው በኋላ “ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ተደስቼበታለሁ። ትልቅ ጦርነት ነበር። ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ተንቀሳቅሰዋል። በተለይ ደግሞ ለማንቸስትር ዩናይትድ ደጋፊዎች ድንቅ ምሽት ነበር” ብለዋል።

የሊቨርፑል መደብዘዝ

ሊቨርፑል ደካማመ አጀማመር አሁንም እንደቀጠለ። ጨዋታው መጀመሩን ከሚያበስረው ፊሽካ መነፋት ጀምሮ በዩናይትድ ተበልጦ አምሽቷል።

የርገን ክሎፕ የተጫዋቾች ጉዳት ተደጋግሞባቸዋል። ዳርዊን ኑኔዝ ደግሞ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

ፋቢንሆ ጨዋታውን በቋሚነት አለመጀመሩ ምስጢር ሆኗል። ጀምስ ሚልነር እና ጆርዳን ሄንደርሰን የነበራቸው ፍጥነት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ሊስተካከል አልቻለም።

የሊቨርፑል ተከላካይ መስመር ክፍተትም ሌላው የታየ ችግር ነው። ቨርጂል ቫን ዳይክ በውድድር ዘመኑ የነበረው ደካማ አቋም ቀጥሏል። የመጀመሪያው ጎልም በእሱ ስህተት የተቆጠረ ነው።

ክሎፕ ከሦስት ጨዋታ ሁለት ነጥብ ብቻ ማግኘታቸው አሳዛኝ ቢሆንም ፍርሃት የሚፈጥር አይደለም።

“መከላከል የነበረብንን ጎሎች አስቆጥረዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የተሻልን በመሆን ችግር ፈጥረንባቸው ነበር። ጥሩ ጥሩ ዕድሎችንም ፈጥረናል። ጨዋታውን በመሸነፋችን ብዙ ምክንያት ማቅረብ አያስፈልግም። በቀጣይ ለራሳችን ስንል እንፋለማለን” ብለዋል ክሎፕ።

ሁለቱም ቡድኖች የአራተኛውን ሳምንት ጨዋታቸውን ቅዳሜ ያከናውናሉ።

ማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ሳውዝሃምፕተን በማቅናት ጨዋታውን ያከናውናል።

ሊቨርፑል በበኩሉ በርንማውዝን በሜዳው አንፊልድ ያስተናግዳል።