በአሜሪካ ኦክላሆማ በሆስፒታል ውስጥ በተከፈተ ተኩስ አራት ሰዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት ቱልሳ በተሰኘች ከተማ ሆስፒታል ውስጥ በተከፈተ ተኩስ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን ፖሊስ ገለጸ።
ትኩስ እንደከፈተ የተጠረጠረው እና ጠመንጃ እና ሽጉጥ ታጥቆ የነበረው ግለሰብ መሞቱንም ፖሊስ አረጋግጧል።
ፖሊስ ጥቃቱ በተሰነዘረበት ቅዱስ ፍራንሲስ ሆስፒታል በሦስት ደቂቃ የደረሰ ሲሆን በጥቃቱ የሚጎዱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ በስፍራው በአስቸኳይ መድረሱ ተገልጿል።
ትላንት ረቡዕ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በርካቶች መቁሰላቸውንም ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
የቱልሳ ከተማ ምክትል የፖሊስ ኃላፊ ኤሪክ ዳላግሊሽ “አሁን ላይ አራት ሲቪል ሰዎች የሞቱ ሲሆን፣ ጥቃት አድራሹም ሞቷል” ብለዋል።
እስካሁን ማንነቱ ያልተለየው ጥቃት አድራሽ እራሱ ሳያጠፋ እንዳልቀረ ተገምቷል።
ተጠርጣሪው ሁለት መሳሪያዎችን ታጥቆ የነበረ ሲሆን “አንደኛው ረዝም ያለ፣ ሌላኛው ደግሞ የእጅ ሽጉጥ ነው በስፍራው የተገኘው” ብለዋል የፖሊስ ኃላፊው።
ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመበት የሆስፒታሉ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የነበሩትን ጨምሮ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞችን ቃል እየተቀበለ ነው።
አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ፖሊስ በስፍራው በደረሰበት ወቅት ጥቂት ሰዎች ቆስለው እና የተወሰኑት ድግሞ ሞተው ነው የደረሰው ብለዋል። በጥቃቱ ስፍራም ከፍተኛ ጉዳት ይታይ ነበር ሲሉም አክለዋል።
ስለክስቱ ለፕሬዝዳንት ባይደን ገለጻ እንደተደረገላቸው ዋይት ሐውስ ባወጣው መግልጫ አመልክቷል።
ከአንድ ሳምንት በፊት በቴክሳስ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 19 ህጻናት እና ሁለት መምህራን መገደላቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው ዕሁድ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ጥቃት እንዳይኖር ድምጻችሁን አሰሙ የሚል ጥሪ አቅርበው ነበር።












