ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ሴቶች እና ወንዶች የተለያየ ሰዓትን መምረጥ እንዳለባቸው ጥናት አመለከተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤና ጠቃሚ እንደሆነ አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን ከምንሰራቸው አካላዊ እንቅስቃሴዎች ተገቢውን ጥቅም እንድናገኝ የምንሰራበትን ሰዓት ከግምት ውስጥ ማስገባት ወሳኝ ነው።
አንድ በቅርቡ የተካሄደ ጥናት፤ ወንዶችና ሴቶች አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ሰዓት የበለጠ ውጤታማ ሊያደርጋቸው እንደሚችል አመላክቷል።
እንደ ጥናቱ ከሆነ ሴቶች ጠዋት ላይ አካላዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኘውን የስብ ክምችት በፍጥነት ማጥፋት የሚችሉ ሲሆን፣ ወንዶችን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርገው ምሽት ላይ ስፖርት መስራታቸው ነው።
በሁለቱም ጾታ ውስጥ የሆርሞን መለያየት፣ የእንቅልፍ ሰዓት እና ተፈጥሯዊ አወቃቀር በጠቅላላው ልዩነት የሚያመጣ መሆኑ በጥናቱ ላይ ተገልጿል።
ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 55 የሆኑና በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ 30 ወንዶችና 26 ሴቶችን ያሳተፈው ይህ ጥናት፤ ለ12 ሳምንታት ነው የተካሄደው።
በእነዚህ ሳምንታት የጥናቱ ተሳታፊዎች የተለያዩ አይነት የማሳሳብ፣ የፍጥነት፣ የጥንካሬ እንዲሁም የዝላይ አቅማቸውን ከፍ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ነበር።
የሴቶቹ ቡድን ከጠዋቱ 2 ሰዓት ተኩል ጀምሮ እነዚህን አካላዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፤ የወንዶቹ ቡድን ደግሞ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት እንቅስቃሴዎቹን እንዲሰሩ ተደርጓል።
ከዚህ በተጨማሪ ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች በልዩ ሁኔታ የተዘጋጁ ምግቦችን እንዲመገቡ ተደርጓል።
ተሳታፊዎቹ በዚህ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ውስጥ ለ12 ሳምንታት የሰነበቱ ሲሆን ተመራማሪዎቹ ደግሞ የደም ዝውውራቸውን፣ በሰውነታቸው ውስጥ ያለውን የስብ መጠን፣ አካላዊ ብቃት እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ሲመዘግቡና ሲያወዳድሩ ቆይተዋል።
መጀመሪያ ላይ ተመራማሪዎቹ ይፋ ያደረጉት ውጤት ሁሉም የጥናቱ ተሳታፊዎች በተለያየ ሰዓት አካላዊ እንቅስቃሴያቸውን ቢያደርጉም ሁሉም በጣም ጥሩ የሚባል አካላዊ ለውጥ አሳይተዋል።
"አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሰዓት መምረጥ ላያስፈልግ ይችላል። ነገር ግን ከሴቶችና ወንዶች አንጻር ስናየው ግን አካላዊ እንቅስቃሴ የምንሰራበት ሰዓት በምናገኘው ጥቅም ፍጥነትና ውጤታማነት ላይ ልዩነት አለው’’ ይላሉ የጥናቱ መሪ የሆኑት ዶ/ር ፖል አርሴሮ።
በጥናቱ መሠረት በሰውነታቸው ውስጥ ያለውን የስብ መጠን መቀነስና የደም ግፊታቸውን ለማውረድ የሚፈልጉ ሴቶች ጠዋት ላይ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ የበለጠ ጥቅም እንደሚያገኙ ዶ/ር ፖል ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አካላዊ ጡንቻቸውን ማሳደግና ጥንካሬያቸውን መጨመር የሚፈልጉ ሴቶች ወደ ማታ አካባቢ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ እንደሚመረጥ ጥናቱ ጠቁሟል።
ወንዶች ደግሞ በጥናቱ መሰረት ጠዋትም ሆነ ማታ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ አጠቃላይ አካላዊ ብቃታቸውን መጨመር የሚችሉ ሲሆን፤ የልባቸውን ጤንነት መጠበቅና ማሻሻል እንዲሁም የአእምሮ ጤና ማሻሻል የሚፈልጉ ከሆነ ግን ማታ አካባቢ አካላዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ ጥሩ ነው።
ወንዶች እና ሴቶች በተለያዩ ሰዓታት አካላዊ እንቅስቃሴን ማድረጋቸው ለምን ልዩነት እንደሚያመጣ ተመራማሪዎቹ እስካሁን አልደረሱበትም። ነገር ግን ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።












