በሩሲያ ጦርነቱን የሚደግፍ ዕውቅ ጦማሪ በቦምብ ጥቃት ተገደለ

VLADLEN TATARSKY/TELEGRAM

የፎቶው ባለመብት, VLADLEN TATARSKY/TELEGRAM

የምስሉ መግለጫ, ጦማሪው ቀንደኛ የጦርነት ደጋፊ ነበር
ታትሟል

በሩሲያ ሴንት ፒተስበርግ ከተማ በፈነዳ ቦምብ አንድ ቀንደኛ የዩክሬን ጦርነት ደጋፊ የሆነ የሩሲያ ጦማሪ ተገደለ።

በፍንዳታው በትንሹ 25 ሰዎች ቆስለዋል።

ፍንዳታውን የሚያሳዩና በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋሩ ተንቀሳቃሽም ምሥሎች ካፌ ከነበሩት ሰዎች በተጨማሪ ደጅ መንገድ ላይ የነበሩ ሰዎችም መጎዳታቸውን ያመላክታሉ።

በብዕር ስሙ ቭላድለን ታታርስኪ የሚባለው ይህ ጦማሪ እውነተኛ ስሙ ማክሲም ፎሚን ነው።

በይበልጥ የሚታወቀው ደግሞ ሩሲያ ዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ደግፎ በሚጽፋቸው መጣጥፎች ነው።

በዚያ ካፌ የተገኘውም በአንድ መርሐ ግብር የክብር እንግዳ ተደርጎ በመጋበዙ ነበር።

የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን ፍንዳታውን በተመለከተ እርስ በእርስ የሚጣረሱ መረጃዎችን ለሕዝብ አሰራጭተዋል።

የአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳለው በመርሐ ግብሩ ላይ ጦማሪ ታተርስኪ በስጦታ መልክ አንድ አነስተኛ የሐውልት ቅርጽ ያላት ጥቅል የተሰጠው ሲሆን ጥቅሏ ውስጥ ቦምብ ተጠምዶ ነበር።

በቴሌግራም የተጋሩ ምስሎች ደግሞ እንደሚያሳዩት ይህ ስጦታ ከተሰጠው በኋላ ጦማሪው ስጦታዋን በተመለከተ ዘለግ ያለ ቀልድ ለታዳሚው ሲያጋራ አሰይተዋል።

ቢቢሲ ሁኔታውን በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

ይህን ጦማሪ ልዩ የሚያደርገው ጦር መሣሪያ አንግቦ ግንባር ድረስ በመሄድ ዘገባዎችን ማጋራቱ ነው።

ባለፈው ዓመት በአንድ የጦር ግንባር ተገኝቶ በሠራው የቪዲዮ ዘገባ ላይ፣ “አንድ በአንድ እናሸንፋቸዋለን፤ አንድ በአንድ እንገድላቸዋለን፣ አንድ በአንድ እንዘርፋቸዋለን፣ አስፈላጊ ከሆንም እንዘርፋቸዋለን፣ እንዳሻን እናደርጋለን።” ሲል ይታያል።

ጦማሪ ታታርስኪ በቴሌግራም ብቻ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ ነበር።

ትናንት ፍንዳታ የተፈጸመበትና ጦማሪው የተገደለበት ካፌ በቅዱስ ፒተስበርግ የሚገኝ ሲሆን ባለቤትነቱ የቀድሞው የዋግነር ቡድን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዚን ነው።

ዋግነር ኩባንያ ለሩሲያ የሚሠራ የቅጥረኛ ገዳዮች ቡድን ነው።

ቅዱስ ፒተስበርግ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ተወልደው ያደጉበትና ለእውቅና የበቁባት ትልቅ ከተማ ናት።

ለቦምብ ጥቃቱ እስከአሁን ኃላፊነት የወሰደ ወገን የለም።

ጥቃቱን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪ ኪካይሎ ፖዶሊያክ እንዳሉት በሩሲያ ሰዎች እርስ በእርስ መበላላት ጀምረዋል፤ ድርጊቱም የአገር ወስጥ ሽብር ነው በማለት አገራቸው እጇ እንደሌለበት አመላክተዋል።