የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የጭስ ቦምብ ጥቃት ተሰነዘረባቸው

የጭስ ቦምቡን ወርውሯል የተባለው ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ሲውል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ በአንድ ሕዝባዊ ዝግጅት ላይ እያሉ የጭስ ቦምብ ተወረወረባቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸውም ከአካባቢው ማስወጣት እንደቻሉም ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ዋካያማ በተባለ ስፍራ ንግግር እያደረጉ በነበረበት ወቅት የጭስ ቦምብ ወርውሯባቸዋል ተብሎ የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የጃፓን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በስፍራው ላይ የነበሩ የዐይን እማኝ አንድ ሰው የሆነ ነገር ሲወረውርና ጭስ ሲወጣ ማየታቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ሌላ የዐይን እማኝ ደግሞ ፍንዳታ እንደሰሙ ተናግረዋል።

ነገር ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በሌሎች ሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።

ፖሊሶች የጭስ ቦምቡን ወርውሯል ተብሎ በታመነው አንድ ግለሰብ ላይ ሲረባረቡ የሚያሳይ ቪዲዮም ወጥቷል።

ተጠርጣሪ የተባለው ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ቢያስታውቅም ተጨማሪ ማብራሪያ ግን አልተሰጠም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ በስፍራው ከፍተኛ ፍንዳታ እንደነበር መናገራቸውን የጃፓን መንግሥታዊ ሚዲያ ኤንኤችኬ ዘግቧል።

“ፖሊስ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ምርመራ እያደረገ ነው። ነገር ግን በዚህ አጋጣሚ በርካታ ሰዎችን ስላስጨነቅኩ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” ማለታቸውም ተዘግቧል።

ኤንኤችኬ በርካታ ሰዎች ከስፍራው ሲሸሹ እንዲሁም ተጠርጣሪው ግለሰብ በፖሊስ ሲወሰድ የሚያሳይ ቪዲዮም አሰራጭቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዋካያማ የሚገኘውን የዓሳ ማጥመጃ ስፍራን ጎብኝተው የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ንግግራቸውን በጀመሩበት ወቅት ነው የጭስ ቦምቡ የተወረወረባቸው። ፉሚዮ ቦምቡ ሳይነካቸው ማምለጥ ችለዋል።

ቦምብ ተወርውሯል የሚል ወሬ መሰማቱን ተከትሎ በአካባቢው ተሰብስቦ የነበረው ሰው ፍንዳታው ከመሰማቱ በፊቱም በድንጋጤ መበታተን እንደጀመረም ተነግሯል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊበራል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አባል የሆኑት ሂሮሺ ሞሪያማ “እንዲህ ያለ ነገር የዲሞክራሲ ዋነኛ መሠረት በሆነው በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት መከሰቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። ይህ ይቅር የማይባል በደል ነው” ብለዋል።

በጃፓን ውስጥ እንዲህ አይነት ጥቃቶች የተለመዱ ባይሆንም፤ ነገር ግን ባለፈው ዓመት በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ላይ እያሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ በአደባባይ በጥይት ከተገደሉ በኋላ በፖለቲከኞች ደኅንነት ዙሪያ ስጋት ነግሷል።