በአፍሪካ አሜሪካዊው ግድያ ምክንያት የሜምፊስ ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲበተን ተደረገ

በኒኮላስ ላይ ድብደባ ፈጽመው ለሞት አብቅተውታል የተባሉት የፖሊስ አባላት

የፎቶው ባለመብት, MPD

የምስሉ መግለጫ, የተበተነው ልዩ የፖሊስ ኃይል በኒኮላስ ላይ ድብደባ ፈጽመው ለሞት አብቅተውታል የተባሉት 5 ፖሊሶች አባል የነበሩበት ነው
ታትሟል

በአሜሪካ ሜምፊስ ውስጥ አንድ አፍሪካ አሜሪካዊ በፖሊሶች በተፈጸመበት ድብደባ ምክንያት ለሞት መዳረጉን ተከትሎ በድርጊቱ የተሳተፉ ፖሊሶች አባል የሆኑትበት የወንጀል መከላከል ቡድን እንዲበተን ተደረገ።

የሜምፊስ ፖሊስ መምሪያ እንዳስታወቀው ታየር ኒኮላስ በተባለው ጥቁር አሜሪካዊ ግድያ የተከሰሱት አምስት ፖሊሶች አባል የሆኑበት ‘ስኮርፒዮን’ የተባለው ልዩ የፖሊስ ቡድን እንዲበተን ተደርጓል።

እንዲበተን የተደረገው ልዩ የፖሊስ ኃይል 50 አባላት ያሉት ሲሆን በከተማዋ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የመቀነስ አላማ ያለው ነበር።

ነገር ግን አምስት የልዩ ኃይሉ አባላት የ29 ዓመቱን ኒኮላስን ከሳምንታት በፊት ሲደበድቡት ከታዩ በኋላ ሕይወቱ በማለፉ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ቁጣን በመቀስቀሱ ቡድኑ እንዲበተን ተደርጓል።

የሟች ቤተሰብ ፖሊስ በወሰደው እርምጃ ደስተኛ መሆናቸውን በጠበቃቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።

የፖሊስ ቡድኑ የተቋቋመው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን በዋናነትም ትኩረት የሚያደርገው በከተማዋ ነዋሪ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አላቸው በተባሉት የመኪና ስርቆት እና በወሮበሎች በሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ ነበር።

ኒኮላስን ለሞት ያደረሰው ድብደባን የሚያሳየው ቪዲዮ ለሕዝብ በፖሊስ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ አምስቱ ጥቁት የፖሊስ አባላትም ከሳምንት በፊት ከሥራቸው ተባረዋል።

የቀድሞ የፖሊስ አባላቱ ሐሙስ ዕለት ለእስር ከተዳረጉ በኋላም አራቱ አርብ ዕለት በዋስ ተለቀዋል።

ፖሊሶቹ በሁለተኛ ደረጃ የግድያ ወንጀል፣ ከባድ ጥቃት በመፈጸም፣ ከባድ የአፈና ድርጊት እና የፖሊስ ደንብን በመጣስ ክሶች ይቀርቡባቸዋል ተብሏል።

በፖሊሶቹ የተፈጸመውን ድርጊት ተከትሎ ፖሊስ መጀመሪያ ላይ እንዳለው ኒኮላስ ከድብደባው በፊት እንዲቆም የተደረገው በግድለሽነት መኪናውን በማሽከርከር ባህሪይ እንደነበረ የተገለጸ ቢሆንም፣ ይህ ክስ በመረጃ የተደረገፈ አልነበረም።

ኒኮላስ በፖሊሶቹ ድብደባ ከተፈጸመበት በኋላ ለሦስት ቀናት በሆስፒታል ቆይቶ ሕይወቱ አልፏል። ሟችም ሆነ አምስቱ ፖሊሶች ጥቁሮች ናቸው።

የሜምፊስ ፖሊስ፣ ፖሊሶቹ የኒኮላስን መኪና ሲያስቆሙ እና ድብደባ ሲፈጽሙበት የሚያሳይ የአንድ ሰዓት የቪዲዮ ምስል አርብ ዕለት ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።

ይህንንም ተከትሎ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ሜምፊስ ውስጥ የተካሄደ ሲሆን፣ አንዳንድ ሰልፈኞችም ዋነኛውን የከተማዋን አውራ ጎዳና ዘግተው ነበር። ትናንሽ የተቃውሞ ሰልፎችም በሌሎች የአሜሪካ ክፍሎች ውስጥ ተደርገዋል።

ሰልፈኞች ለሟች ኒኮላስ ፍትሕ እና በፖሊስ ይፈጻማል ያሉት “ሽብር” እንዲቆም የሚጠይቁ ጽሁፎችን ይዘው ወጥተዋል።

ግድያውን እና የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ እንዲበተን የተደረገው ልዩ የፖሊስ ኃይል ከባድ ወንጀሎችን በመከላከል እና ወንጀል ፈጻሚዎችን ለመያዝ እንደቻለ ይነገርለታል።

ነገር ግን አንዳንድ የቡድኑ አባላት በነዋሪዎች ላይ በሚፈጽሟቸው ድርጊቶች የተነሳ አለመግባባቶች እየተፈጠሩ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ።