ቻይናዊው መሃንዲስ አሜሪካ ውስጥ በስለላ ተከሶ ስምንት ዓመት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካንን የአቪየሽን ንግድ ምስጢሮች ለመስረቅ ከተደረገ ጥረት ጋር በተያያዘ አንድ ቻይናዊ መሃንዲስ በስለላ ተከሶ የስምንት ዓመት አስር ተፈረደበት።
የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት እንዳለው የ31 ዓመቱ ጂ ቻኦኩን የአገሪቱን ምስጢሮች ለማሾለክ ይረዳሉ ያላቸውን ሳይንቲስቶች እና መሃንዲሶችን ለመመልመን ለይቶ ይዞ ነበር።
በተጨማሪም መሃንዲሱ ለመልማዮች ሐሰተኛ መረጃን በመስጠት በአሜሪካ ተጠባባቂ ሠራዊት ውስጥ አባል ሆኖ ተመልምሎ ነበር።
ጂ የስለላ ሥራውን ሲያከናውን የነበረው ከቻይና ቁልፍ የደኅንነት ክፍል መመሪያዎችን እየተቀበለ እንደሆነ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
ለአሜሪካ ሠራዊት ሐሰተኛ ቃል በመስጠት እና ለዐቃቤ ሕግ ሳየሳውቅ የለውጭ መንግሥት ወኪል ሆኖ እየሰራ መሆኑ ባለፈው መስከረም የስለላ ክስ እንዲከፈትበት አድርጓል።
ጂ ከአስር ዓመት በፊት በተማሪ ቪዛ ወደ አሜሪካ የገባ መሆኑን የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ግለሰቡ የጂያንግሱ ግዛት የአገር ደኅንነት ሚኒስቴር ለተባለው አካል ሊመለመሉ የሚችሉ ስምንት ሰዎችን በተመለከተ መረጃን አሳልፎ በመስጠት ተከሷል።
ለምልመላው መረጃቸው የተሰበሰበው ግለሰቦች ሁሉም ትውልዳቸው ከቻይና ወይም ከታይዋን ቢሆንም የአሜሪካ ዜግነትን ያገኙ ናቸው። አንዳንዶቹም ለአሜሪካ የመከላከያ መሥሪያ ቤት በኮንትራክተርነት የሚሰሩ ናቸው ተብሏል።
ጂ ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም የሚያገለግል ክህሎት ያላቸው የውጭ ዜጎች እንዲመለመሉ በወጣው ፕሮግራም መሠረት በ2016 (እአአ) ነበር በአሜሪካ ተጠባባቂ ሠራዊት ውስጥ የተካተተው።
በምልመላው ማመልከቻ ላይም ሆነ በሰጠው ቃል ላይ ቀደም ባሉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ከውጭ መንግሥት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳላደረገ ዋሽቶ እንደነበር የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ነገር ግን አንድ የአሜሪካ የደኅንነት ስውር አባል የቻይና መንግሥት የደኅንነት ሚኒስቴር ተወካይ መስሎ ከቀረበው በኋላ፣ በተገኘበት መረጃ ምክንያት በ2018 (እአአ) በቁጥጥር ስር ውሏል።
ጂ ከአሜሪካው የደኅንነት ሠራተኛ ጋር በተገናኘባቸው ጊዜያት፣ ባለው የሠራዊት አባልነት መታወቂያው በመጠቀም አውሮፕላን ተሸካሚ መርከቦችን መጎብኘት እና ፎቶ ማንሳት እንደሚችል ነግሮታል።
በተጨማሪም አንድ ጊዜ የአሜሪካ ዜግነቱን ካገኘ እና የደኅንነት ምርመራን ካለፈ በኋላ ሲአይኤ፣ ኤፍቢአይ ወይም ናሳ ውስጥ ሥራ ለማግኘት እንደሚሞክር ገልጿል።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንዳሉት ጂ በተቋሞቹ በአንዳቸው ውስጥ የመረጃ መረብ ደኅንነት ሥራ በማግኘት የሳይንሳዊ መርምር መረጃዎችን ጨምሮ ወደ መረጃ ቋቶቻቸው ለመግባት የሚያስችል ዕድልን ለማግኘት ዕቅድ ነበረው።
ባለሥልጣናቱ ጨምረውም ጂ ትዕዛዝ ሲቀበል የነበረው በአሜሪካ ውስጥ ለፍርድ እንዲቀርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተላልፎ ከተሰጠው ታዋቂ ከፍተኛ የቻይና የደኅንነት መኮንን ከዡ ያንጁን ነበር።
ጄኔራል ኤሌክትሪክን ጨምሮ ከአሜሪካ ከአየር በረራ እና የህዋ ጉዞ ኩባንያዎች የንግድ ምስጢሮችን ለመስረቅ በማሴር ዡ ባለፈው ዓመት የ20 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ከሳምንታት በፊት ደግሞ የጄኔራል ኤሌክትሪክ ሠራተኛ የነበረው ዤንግ ዢያኩንግ ከሚሰራበት ኩባንያ ለቻይና መንግሥት ምስጢራዊ መረጃዎችን አሳልፎ በመስጠት የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ባለፈው ዓመት ሐምሌ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ራይ፣ ቻይና የምዕራባውያን ኩባንያዎችን አእምሯዊ ንበረቶችን “በመዝረፍ” ኢንዱስትሪያዊ ልማቷን አፋጥና የዓለምን ቁልፍ ዘርፎችን በበላይነት ለመቆጣጠር አቅረዳ እየሰራች ነው ብለዋል።
ነገር ግን ቻይና ለዳይሬክተሩ ክስ በሰጠችው ምላሽ “የቻይናን ስም ማጥፋት ነው” በማለት ባለሥልጣኑ አሁንም “የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት አስተሳሰብን ያራምዳሉ” ስትል አጣጥላዋለች።












