በካናዳ 10 ሰዎችን በስለት ከገደሉ ተጠርጣሪዎች ሌላኛውም በፖሊስ ከተያዘ በኋላ ሕይወቱ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በካናዳ 10 ሰዎችን በስለት ወግቶ በመግደልና 18 ሰዎች ላይ ጉዳት በማድረስ ከተጠረጠሩት ሁለት ወንድማማቾች ውስጥ አንደኛው ሞቶ ከተገኘ ከቀናት በኋላ ሌላኛውም በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ ሕይወቱ አለፈ።
ፖሊስ እንዳለው የ32 ዓመቱ ማይልስ ሳንደርሰን ረቡዕ ከሰዓት በኋላ በሳስካቸዋን ግዛት ከፍተኛ ክትትል ከተደረገበት በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር።
ከአካባቢው የወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል በሮስተርን ከተማ አቅራቢያ ነጭ የስፖርት መኪና (ሱቭ) ተሽከርካሪ ከመንገድ ስትወጣ እና በፖሊስ ስትከበብ አሳይቷል።
እሁድ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት ከተገደሉት ባሻገር አስር ሰዎች ሆስፒታል የገቡ ሲሆን ሦስቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
የግዛቷ ረዳት ኮሚሽነር ርሆንዳ ብላክሞር ረቡዕ ምሽት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ “ግዛታችን የእፎይታ አየር እየተነፈሰች ነው” ብለዋል።
ተጠርጣሪው ማይልስ ሳንደርሰን ቀደም ብሎ ከአንድ ግቢ ውስጥ ተሽከርካሪ እንደሰረቀ ጥቆማ እንደደረሳት የተናገረችው ረዳት ኮሚሽነሯ፣ የቤቱ ባለቤት ላይ ግን ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ ተናግራለች።
ፖሊስ በሚከታተለው ጊዜም ማይልስ 150 ኪሎ ሜትር በሰዓት እያሽከረከረ ነበር ። በፖሊስ ክትትል ከመንገድ እንደወጣ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል። ማይልስ ሲያሽከረክረው በነበረው መኪና ውስጥም ስለት መገኘቱን የፖሊስ ኃላፊዋ አስታውቀዋል።
ይሁን እንጂ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ ብዙም ሳይቆይ ማይልስ ህመም አጋጥሞት ሳስካተን ወደሚገኝ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
ረዳት ኮሚሽነሯ ፣ የሞቱ መንስዔ ከአስክሬን ምርመራ በኋላ እንደሚታወቅ በመግለጽ ተጨማሪ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቀደም ብሎ ስማቸው ያልተገለጸ ባለሥልጣን ግን ማይልስ ራሱ ላይ ጉዳት በማድረሱ መሞቱን ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
የማይልስ በፖሊስ የመያዝ ዜና የተሰማው፣ ስለት የታጠቀ ግለሰብ መኪና እያሽከረከረ በመታየቱ በዋካው ከተማ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ራሳቸውን በተገቢው ቦታ እንዲጠልሉ ወይም ቤታቸው ውስጥ እንዲሆኑ የማስጠንቀቂያ መልዕክት በካናዳውያን ሞባይል ስልክ ከተላከ በኋላ ነበር።
ማይልስ በመጀመሪያ ደረጃ ግድያ ፣ በግድያ ሙከራ እና ቤት ሰብሮ በመግባት ክስ ይጠብቀው ነበር።
ወንድሙ ዴሜን ሳንደርሰንም እሁድ ዕለት በተፈፀመው ጥቃት ተሳትፏል በሚል ክስ ቀርቦበት ነበር።
ይሁን እንጂ ሰኞ ዕለት ፖሊስ ሕይወቱ አልፎ አግኝቶታል። ፖሊስ ወንድሙን በሚከታተለው ጊዜ ወንድሙ ገድሎት ይሁን አይሁን ለማወቅ ምርምራ እየተካሄደ ነው።
ረቡዕ ዕለት የሁለቱ ወንድማማቾች ወላጆች በሕይወት የተረፈው ልጃቸው እጁን እንዲሰጥ ተማፅነው ነበር።
እናታቸው ከሲቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ላይ “ በልጆቼ ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ። የሆነውን ሁሉ አናውቅም። ነገር ግን በዚህ ጥቃት የተጎዳችሁ እና ለችግር የተዳረጋችሁትን ሁሉ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ፖሊስ እስካሁን በስለት ጥቃት የፈፀሙ ተጠርጣሪዎች ዓላማ ምን እንደሆነ አልገለጸም። እስካሁን 13 ወንጀሎች የተፈፀሙ ሲሆን አብዛኞቹ ተጠርጣሪዎችም ተገድለዋል።
የካናዳ የይቅርታ ቦርድ ማክሰኞ እለት ማይልስ ሳንደርሰን ለፈፀማቸው በርካታ ወንጀሎች የአራት ዓመት እስር ከተፈረደበት በኋላ ቀደም ብሎ ለምን እንደተፈታ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ቦርዱ የካቲት ወር ላይ የማይልስ ከእስር መለቀቅ በማኅበረሰቡ ላይ ተጨማሪ ወንጀል እንዲፈፀም መፍቀድ ነው ሲል ይቅርታ እንደማያደርግ ገልጾ ነበር።
የይቅርታ ቦርዱ እንዳለው ማይልስ ሳንደርሰን ከ18 ዓመት እድሜው ጀምሮ ዝርፊያ፣ ትንኮሳ እና ማስፈራራትን ጨምሮ 59 ክሶች ቀርበውበት ተፈርዶበት ነበር።
የሳስካቶን ፖሊስም ቀደም ብሎ ከግንቦት ወር ጀምሮ ማይልስ ሳንደርሰንን ሲፈልግ እንደነበር ገልጿል።












