ካናዳ፡ በስለት 10 ሰዎችን ከገደሉ ሁለት ተጠርጣሪዎች አንዱ ሞቶ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, RCMP SASKATCHEWAN
የካናዳ ፖሊስ እሑድ ዕለት በሳስካቹዋን ግዛት በተፈፀመው የጅምላ ጥቃት ጀርባ ከሚገኙ ሁለት ተጠርጣሪዎች አንዱ ህይወቱ አልፎ መገኘቱን ገለጸ።
የ31 ዓመቱ የዴሚየን ሳንደርሰን አስከሬን በጄምስ ስሚዝ ክሪ ኔሽን መገኘቱ ታውቋል። አካባቢው የበርካታ ተጎጂዎች መኖሪያ ነው ተብሏል ።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ወንድማማቾች ናቸው። ፖሊስ እንዳለው ከሆነ ሚልስ ሳንደርሰን አሁንም በቁጥጥር ስር ያልዋለ ሲሆን እና በሪጂና ከተማ እንደሚገኝ ይታመናል።
በካናዳ ታሪክ ውስጥ ከታዩት አስከፊ ጥቃቶች አንዱ በሆነው የእሑዱ ድርጊት 10 ሰዎች በስለት ተወግተው ተገድለዋል።
በጥቃቱ ሌሎች 18 ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃቱ የተፈፀመው በሳስካቹዋን ግዛት ውስጥ ነው።
ተጠርጣሪዎቹ ለመጨረሻ ጊዜ በታዩባት የግዛቲቱ ዋና ከተማ በሆነችው ሬጂና የተጎጂ ቤተሰቦች ሐዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
ሰኞ አመሻሹ ላይ በከተማው እምብርት ላይ ሁለተኛውን ተጠርጣሪ ለማደን የሚደረጉ ምንም ግልጽ ምልክቶች አልታዩም።
የላብ አደሮችን ቀን በመሆኑ ከተማዋ ጸጥ ረጭ ብላ ውላለች።
የሚታየው ጸጥታ ከተንቀሳቃሽ ስልክ በተደጋጋሚ በሚደርስ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ይረበሻል። መልዕክቱ ስለሁለቱ ጥቃት አድራሾች ይገልጻል።
ከሳስካቹዋ ፣ ማኒቶባ እና አልበርታ የተወጣጡ መኮንኖች በፍለጋው ላይ ተሰማርተዋል።
የጥቃት መስፋፋት በተለምዶ ሠላማዊ የሚባለውን ግዛት አናውጦታል።
ፖሊስ 13 የተለያዩ የወንጀሎችን እየመረመረ ይገኛል።
ዴሚየን እና ማይልስ በቁጥጥር ስር ባይውሉም በግድያ ወንጀል ተከሰው ነበር።
የፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ሮንዳ ብላክሞር እንደተናገሩት ጀምስ ስሚዝ ክሪ ኔሽን በሚባለው አካባቢ የወንድ አስከሬን ተገኝቷል።
በኋላም "ሟቹ ዴሚየን ሳንደርሰን እንደሆነ” ተረጋግጧል ብለዋል።
“አስከሬኑ በሳር በተሸፈነ አካባቢ ከቤት ውጭ መገኘቱን እና በባለሥልጣናት እየመረመሩት ካለው ቤት በቅርብ ርቀት የሚገኝ ቦታ ነው” ብለዋል።
ብላክሞር አክለውም የዴሚን አስከሬን “በግልጽ የሚታዩ ጉዳቶች ያሉበት” ሲሆን “ራሱ ላይ ጉዳት ያደርሳል ተብሎ አይታመንምም” ብለዋል።
የዴሚየን ወንድም ማይልስ በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ ፖሊስ አስታውቆ አደገኛ ግለሰብ በመሆኑ ሰዎች አካባቢያቸውን በንቃት አንዲከታተሉ ጠይቋል።
የ30 ዓመቱ ተጠርጣሪም ጉዳት ደርሶበት ሊሆን ይችላል ተብሏል። የህክምና እርዳታ ሊጠይቅ ይችላል ሲል ፖሊስ አስጠንቅቋል። ለወንድሙ ሞት ተጠያቂው እሱ ስለመሆኑ ምንም አልገለጸም።
ቀደም ሲልም በፖሊስ ይታወቅ የነበረው ማይልስ በግለሰቦች እና በንብረት ላይ በተፈፀመ ወንጀል ከበርካታ ዓመታት በፊት "ሰፋ ያለ እና ረዥም ወንጀል" እንደነበረው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ "ይህ አይነት ጥቃት በሓገራችን ቦታ የለውም" ሲሉ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል።
“እንዲህ ያሉ አሳዛኝ ሁኔታዎች በጣም የተለመዱ ነገሮች ሆነዋል” ብለዋል።
ሳስካቹዋናውያን እና ካናዳውያን በዚህ ዓይነቱ “የችግር እና የጭንቀት ጊዜ” እንደሚደጋገፉም ተናግረዋል ።
ብዙዎቹ ተጎጂዎች ወደ 2,000 የሚጠጉ ሰዎች የሚኖሩበት የጄምስ ስሚዝ ክሪ ኔሽን ነዋሪዎች ናቸው። በሳስካቹዋን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል።
የካናዳ መገናኛ ብዙሃን የተወሰኑትን ተጎጂዎች ለይተዋል። በጉዳዩ ላይ ባለስልጣናት ይፋዊ መረጃ አልሰጡም።












