በሲሲሊ በሰጠመችው መርከብ ተሳፍረው የነበሩ የዩኬ ቱጃሮች መጥፋታቸው ተነገረ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በሲሲሊ በተነሳ ማዕበል በሰጠመችው ቅንጡ መርከብ ተሳፍረው የነበሩ የዩኬ ቱጃሮች መጥፋታቸው ተነገረ።

ከነዚህም ውስጥ የብሪቲሽ ቢል ጌት በመባል የሚታወቀው የቴክኖሎጂ ፈጣሪው ማይክ ሊንች፣በትሪሊዮኖች ዶላር የሚቆጣጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅሰው ሞርጋን ስታንሊ የተሰኘው አለም አቀፉ ባንክ ኃላፊ ጆናታን ብሉመር ይገኙበታል።

ከነዚህ ግለሰቦች በተጨማሪም ታዋቂው ጠበቃ ክሪስ ሞርቪሎ አደጋውን ተከትሎ ደብዛቸው ከጠፉ ሰዎች ተካትተዋል።

ቅንጡዋ መርከብ በሲሲሊ ሰኞ ዕለት በደረሰባት የማዕበል አደጋ መስጠሟን የሲሲሊ የሲቪል ጥበቃ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ከሜድትራንያን ደሴት ዳርቻ 700 ሜትር ርቀር በደረሰው አደጋ ከ59 ዓመቱ ማይክ ሊንች በተጨማሪ የ18 ዓመቱ ልጁ ያለችበት አልታወቀም።

56 ሜትር እርዝማኔ ያላት ቅንጡዋ መርከብ ከብሪታንያ ዜጎች በተጨማሪ አሜሪካውያን እና ካናዳውያን ጨምሮ 22 ሰዎችን አሳፍራ ነበር።

እስካሁን ድረስ 15 ተሳፋሪዎችን መታደግ የተቻለ ሲሆን የመርከቧ የምግብ አብሳይ አስክሬን መገኘቱን የሲሲሊ ሲቪል ጥበቃ ገልጿል።

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 14/ 2016 ዓ.ም የማፈላለግ ስራው እንደቀጠለም የጣሊያን ሚዲያዎች ዘግበዋል።

12 ተሳፋሪዎችን እና 10 ሰራተኞችን የያዘችው ባለ ብሪታንያዋ ሰንደቅ ዓላማ ቅንጡ መርከብ ሰኞ ዕለት ነው ከሲሲሊ ዋና ከተማ ፓሌርሞ በስተምስራቅ በምትገኘው ፖርቲሴሎ ወደብ አቅራቢያ የሰጠመችው።

መርከቧ በኃይለኛ ማዕበል ከተመታች ሚዛኗን አጥታ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት መስጠሟ ተገልጿል።

ሰኞ እለት ልዩ የእሳት አደጋ ሰራተኞች እንዲሁም ጠላቂ የነፍስ አድን ሰራተኞች ከሮም መጥተው ከባህር ወለል በታች 50 ሜትር ርቀት ላይ ያደረጉት የመጀመሪያ ፍለጋ አልተሳካም ነበር።

ደብዛቸው ከጠፉ ተሳፋሪዎች አንዱ የሆነው ማይክ ሊንች አንዳንዶች “የብሪታንያው ቢል ጌትስ” ሲሉ ነው የሚጠሩት።አውቶኖሚ የሚባል የሶፍትዌር ኩባንያን በጋራ የመሰረተው ማይክ በአውሮፓውያኑ 2011 ለአሜሪካዊው ግዙፍ ኩባንያ ሄውለት ፓካርድ በ11 ቢሊዮን ዶላር ሽጦታል።

ነገር ግን ከሽያጩ ጋር በተገናኘ ተፈጽሟል በተባለ የማጭበርበር ክስ ከአስር ዓመት በበለጠ የፍርድ ሂደት ውስጥ ቆይቷል። ቱጃሩ በሰኔ ወር ውስጥ በአሜሪካ ከቀረቡበት የተለያዩ የማጭበርበር ክሶች በነጻ ተሰናብቷል።

ከረጅም አመታት በኋላ በነጻ የተሰናበተው ማይክ ሊንች ይህንንም ደስታ ምክንያት በማድረግ የህግ ባለሙያ ቡድን አባሎቹን ወደ መርከቧ እንደጋበዘ የሚገልጹ ዘገባዎች ወጥተዋል። በዚሁ በማጭበርበር ክስ ተመስርቶበት የነበረው ስቴፈን ቻምበርሊን ቅዳሜ ዕለት በካምብሪጅሻየር በመኪና ተገጭቶ መሞቱ በጠበቃው በተረጋገጠበት እለት ነው የመርከቧ አደጋ የተሰማው።

ሌላኛው ደብዛቸው ጠፍቷል የተባሉት ታዋቂው ጠበቃ ክሪስ ሞርቪሎ አንደኛው ናቸው።

ክሪስ የቱጃሩን ማይክ ሊንችን የፍርድ ሂደትን ጨምሮ ከፍተኛ የሙስና ጉዳዮች ላይ የተሳተፉ የህግ ባለሙያ ናቸው። በአውሮፓውያኑ 2001 በአሜሪካ በዓለም ንግድ ማዕከል ላይ በተፈጸመው የአሸባሪዎች ጥቃት ዙሪያ በወንጀል ምርመራ ላይ ከአውሮፓውያኑ 1999 እስከ 2005 በኒውዮርክ በረዳት አቃቤ ህግነት ሰርተዋል።

የሞርጋን ስታንሊ ኢንተርናሽናል ባንክ ኃላፊ ጆናታን ብሉመር ሌላኛው ከጠፉት ስድስት ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

የ70 ዓመቱ ጆናታን ሂስኮስ የተሰኘ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሊቀመንበር ናቸው፥

ቅንጡ መርከቧ ሬቭቶም ሊሚትድ የተሰኘ ኩባንያ ባለቤትነት የተመዘገበች ሲሆን የዚህ ኩባንያ ባለቤትም የቱጃሩ ማይክ ባለቤት አንጄላ ባካሬስ መሆኗ ተገልጿል።