ኢራን በቅርቡ እስራኤል ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች ብለው እንደሚጠብቁ ባይደን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ኢራን በቅርቡ እስራኤል ላይ ጥቃት ትሰነዝራለች ብለው እንደሚጠብቁ ተናገሩ።
ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ኢራን በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ የጦር አዛዦቿ ለተገደሉበት የአየር ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ትሰጣለች የሚለው ስጋት ባየለበት ወቅት ነው።
እስራኤል በሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ለተፈፀመው ጥቃት ኃላፊነት ባትወስድም ከጥቃቱ ጀርባ እንዳለችበት ይታመናል።
በዚህም ምክንያት በቅርቡ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሊፈፀም እንደሚችል የአሜሪካ ባለሥልጣናት የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።
እስራኤል በበኩሏ ራሷን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆነች ገልጻለች።
ባይደንም ኢራን ጥቃት እንዳትፈፅም አስጠንቅቀዋል። “ እስራኤልን ለመከላከል ቁርጠኛ ነን። እስራኤልን እንደግፋለን። እስራኤል ራሷን እንድትከላከል እንረዳታለን። በመሆኑም ኢራን አይሳካላትም “ ብለዋል ፕሬዚደንት ባይደን።
በኢራን የሚደገፈውና በጋዛ እስራኤልን እየተዋጋ ያለው የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሐማስ እንዲሁም በሌባኖስ የሚንቀሳቀሰውን ሔዝቦላህን ጨምሮ በቀጠናው ያሉ ሌሎች ደጋፊ ቡድኖችም በእስራኤል ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈፅመዋል።
አርብ ዕለት ሔዝቦላህ ከሌባኖስ ወደ እስራኤል በርካታ ሮኬቶችን እንደተኮሰ ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ቃል አቀባይም 40 ሚሳይሎች እና ሁለት ፈንጂ ድሮኖች መተኮሳቸውን ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት የደረሰው ጉዳት ያልተገለጸ ሲሆን የሌሎች አካላት እጅ እንዳለበት የሚጠቁም መረጃም የለም።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሲቢኤስ እንደተናገሩት ይህ ድብደባ ኢራን በእስራኤል ላይ ትፈፅመዋለች ተብሎ ከሚጠበቀው ጥቃት የተለየ ነው።
የቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር ኢራን ሆነ ብላ መካከለኛው ምስራቅን እና የዋሽንግተንን ግምት እየጠበቀች ነው ብሏል።
እስራኤል፣ ኢራን በሌባኖስ እና ሶሪያ ላሉ ወኪሎቿ በስውር የጦር መሣሪያ እያቀረበች ነበር ብላ ባመነችበት እና በደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ጥቃት ከተፈፀመ በኋላ የኢራን የደኅንነት ተቋም ስለሚፈፅመው የአፀፋ እርምጃ ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ሆኖም ኢራንም ሆኑ በባሕረ ሰላጤው ያሉ ጎረቤቶቿ ሰፊ ጦርነት ማካሄድ አይፈልጉም።በባሕር ሰላጤው ያሉ አገራትም ኢራን ትፈፅመዋለች ከተባለው ጥቃት እንድትታቀብ አስቀድመው ጠይቀዋል።
ይህን ውጥረት ተከትሎ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሕንድ እና አውስትራሊያን ጨምሮ ሌሎች አገራት ዜጎቻቸው ወደ እስራኤል ጉዞ እንዳያደርጉ አስጠንቅቀዋል።
ጀርመንም ዜጎቿ ኢራንን ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትም በእስራኤል የሚገኙ ዲፕሎማቶች እና ቤተሰቦቻቸው ከቴል አቪቭ፣ እየሩሳሌም እና ቢርሽባ ውጭ እንዳይንቀሳቀሱ አግዷል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ደግሞ በእነዚህ ሁሉ ማሳሰቢያዎች ውስጥ የጦር ካቢኔ አባላቶቻቸው ጋር ተገናኝተዋል።
አንዳንድ እስራኤላውያን ኢራን ትፈፅመዋለች የተባለው ጥቃት እንዳላስጨነቃቸው ገልጸዋል።
ዳንኤል ኮስማን የተባለ እስራኤላዊ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ሲናገር “ በሁሉም አቅጣጫ በጠላቶች እንደተከበብን እናውቃለን፤ ግን አልፈራንም። አካባቢውን ተመልከት ሰዎች እየተንቀሳቀሱ ነው” ብሏል።
የእስራኤል መንግሥት ለሕዝቡ ለሦስት ቀናት የሚሆን ውሃ፣ ምግብ እና መድሃኒት እንዲያዘጋጁ ከመንገር ባለፈ አዲስ የሰጠው ምንም ዓይነት መመሪያ የለም።
ሆኖም የአካባቢ ባለሥልጣናት የመጠለያዎችን ዝግጁነት መገምገምን ጨምሮ ሊፈፀም ለሚችለው ጥቃት እየተዘጋጁ እንደሆነ መናገራቸውን የእስራኤል ራዲዮ ዘግቧል።
ባለፈው ሳምንትም የእስራኤል ጦር ለወታደሮቹ የሚሰጠውን እረፍት ሰርዟል። የአየር መከላከያውንም ያጠናከረ ሲሆን ተጠባባቂዎችንም ጠርቷል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በደማስቆ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ በተፈፀመው ጥቃት 13 ሰዎች ተገድለዋል።
ይህም ከፍተኛ የኢራን የጦር መሪዎችን የሚጨምር ሲሆን ከእነዚህ መካከል በሶሪያ እና በሌባኖስ የሚንቀሳቀሰው የኢራን ኩድስ ኃይል አዛዥ ብርጋዲየር ጀኔራል መሐመድ ሪዛ ዛሄዲ ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የበርካታ አገራት ባለሥልጣናት ጦርነቱ ወደ ሌሎች አገራትም ይስፋፋል በሚል ስጋት ኢራን ጥቃት እንዳትፈፅም ለማግባባት እየሞከሩ ነው።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር አንቶኒ ብሊንከን በኢራን ላይ ጫና እንዲፈጥሩ ከቻይና፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ ሚኒስትሮች ጋር ተነጋግረዋል።
የጋዛው ጦርነት የተቀሰቀሰው ሐማስ የእስራኤልን ድንበር ጥሶ በመግባት 1 ሺህ 200 ሰዎችን ከገደለ እና 250 ሰዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ነበር።
እስራኤል ከታገቱት ሰዎች መካከል 130 የሚሆኑት አሁንም በጋዛ እንደሚገኙና ቢያንስ 34ቱ እንደሞቱ ገልጻለች።
በሐማስ እንደሚመራው የጤና ሚኒስቴር ከሆነ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እስካሁን ከ33 ሺህ 600 በላይ የጋዛ ዜጎች ተገድለዋል።
ይህ ግጭት እስራኤል በሰሜናዊ ድንበሯ በኩል በየቀኑ ከሔዝቦላህ ጋር የተኩስ ልውውጥ እንድታደርግ አድርጓል።
በኢራቅ እና በየመን የሚገኙ በኢራን የሚደገፉ ቡድኖችም የእስራኤልን ግዛት እንዲሁም በኢራቅ እና በሶሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ለመምታት ሞክረዋል።
የየመን ሁቲዎችም በቀይ ባሕር ላይ መርከቦች ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን ቢያንስ አንድ መርከብ ሰምጧል። ይህም አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም በየመን የሁቲ አማጺያንን ኢላማ ያደረገ የአየር ጥቃት እንዲፈፅሙ አድርጓቸዋል።












