ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ በዩክሬኗ ከተማ የውሃ አቅርቦትን ሆን ብላ ቆርጣለች የሚል ክስ ቀረበባት
ለስድስት ወራት ያህል በዩክሬን ደቡባዊ የባህርደ ዳርቻ ከተማ ማይኮላይቭ ያሉ ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የላቸውም።
ወታደራዊ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሙያዎች ባለፈው ሚያዚያ ወር የሩስያ ሃይሎች የውሃ አቅርቦቱን አቋርጠዋል ብለው እንደሚያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሳተላይት ምስሎች እና መረጃዎች ወደ ከተማዋ የሚወስደው የቧንቧ መስመር በሩሲያ ቁጥጥር ስር እያለ ሆን ተብሎ መውደሙን አሳይቷል።።
ለሰላማዊ ሰዎች አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን ማውደም የአለም አቀፍ የሰብአዊ ህግ ጥሰት ተደርጎ ይወሰዳል።
ነገር ግን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ሩሲያ በዩክሬን የኃይል እና የውሃ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በሰፊው እየፈፀመች ሲሆን ይህም በመላ አገሪቱ መስተጓጎል እንዲፈጠር አድርጓል።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ ለማግኘት በማይኮላይቭ መንገድ ላይ መውጣት ከተማዋ የጦር ቀጣና በመሆኗ አደገኛ ነው። ከተማዋ ከሩሲያ ወረራ ጀምሮ በዩክሬን ቁጥጥር ስር ሆና ቆይታለች።
“ወደ ውጭ መውጣት በጣም ያስፈራል። አንድ ነገር ከሰማይ መጥቶ የሚመታን ነው የሚመስለን” በማለት በሩሲያ ቁጥጥር ስር ከምትገኘው ኬርሶን ክልል ወደ ማይኮላይቭ የሸሸች የ36 አመቷ እናት አንያ ትናገራለች።
ሌሎች አራት የቤተሰቧን አባላት የሚንከባከቡ እንደ አኒያ ያሉ ነዋሪዎች በቤታቸው ውስጥ ቴክኒካል ተብሎ የሚጠራ ውሃ ያገኛሉ ነገር ግን ውሃው ለመጠጥም ሆነ ለማብሰል መጠቀም አይቻልም።
በዚህ ውሃ ገላ መታጠብ ቆዳን የሚያንገበግብ ሲሆን “በጣም ጨዋማ ነው። ቡናማ እና አረንጓዴ ቀለም አለው” ትላለች።
የከተማው የውሃ አቅርቦት ከተቋረጠ በኋላ ነዋሪዎች ለስድስት ወራት ያህል እንደዚህ ባለ ፈታኝ ሁኔታ እያለፉ ይገኛሉ።
ይህ በሩሲያ ኃይሎች ሆን ተብሎ የተደረገ ድርጊት መሆኑን በቢቢሲ የተሰበሰቡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ አንድ የዩክሬን የዜና ማሰራጫ ምስሎች አሳትሞ በማይኮላይቭ ብቸኛው የውሃ ማስተላለፊያ ላይ በሩሲያ ሃይሎች የደረሰበትን ውድመት ያሳያል።