ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ ‘የዩክሬን ህጻናት ይቃጠሉ’ ያለውን ታዋቂ ጋዜጠኛ ከሥራ አገደች
አንቶን ክራሶቭስኪ የሩስያ መንግሥት በሚያስተዳድረው አርቲ የተሰኘው መገናኛ ብዙሃን ታዋቂ የቴሌቭዥን አቅራቢ ነው።
ጋዜጠኛው “የዩክሬን ህጻናት እንዲቃጠሉ እና እንዲሰምጡ” መጠየቁን ተከትሎ ከሥራው ሲታገድ ጣቢያውም ጉዳዩን አውግዞታል።
በቴሌቭዥን የሰጠው አስተያየት በማህበራዊ ድር አምባዎች ውግዘትን የቀሰቀሰ ሲሆን በኋላም ይቅርታ ጠይቋል።
እአአ በ1980 በምዕራብ ዩክሬን ህጻናት "ዩክሬን በሞስኮባውያን ተይዛለች" ሲሉ ሰማሁ ሲል የሳይንስ ልብ ወለድ ጸሐፊው ሰርጌይ ሉክያኔንኮ ሲል ለተናገረው ነው ክራሶቭስኪ ምላስ የሰጠው።
አርቲ ኒውስ ቀንደኛ የክሬምሊን ደጋፊ ነው።
በቃለ መጠይቁ ወቅት ክራሶቭስኪ ፈገግ እያለ "እነዛን ልጆች ብቻ አስጥሟቸው፣ አስጥሟቸው" ብሏል። “ወይም ደግሞ ወደ ጎጆ ተወርውረው ይቃጠሉ” ሲልም አማራጭ አቅርቧል።
የሩስያ ወታደሮች የዩክሬን አያቶችን ስለመደፈራቸው እያነሳም ቀልዷል።
የአርቲ ዋናአዘጋጅ ማርጋሪታ ሲሞንያን የክራሶቭስኪን አስተያየት "ያልተገራ እና አስጸያፊ" በማለት አውግዘዋል።
ዩክሬን ጣቢያው የዘር ማጥፋት ወንጀል ያነሳሳል ስትል ትከሳለች። የሩሲያው ቴሌቪዥን በዩክሬን ላይ የሚደረገውን ጦርነት አጥብቀው ለሚደግፉ እና ጠንካራ ወታደራዊ ጥቃት ይካሄድ ለሚሉ ምሁራን እና አቅራቢዎች ብዙ የአየር ጊዜ ሰጥቷል። የክሬምሊንን አቋም በማስተጋባት በዩክሬን “የተፈበረኩ” ናቸው በማለት የሩሲያ የጭካኔ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ውድቅ ያደርጋሉ።
ከባድ ወንጀሎችን የሚመለከተው የሩሲያ የምርመራ ኮሚቴ የክራሳቭስኪን አስተያየት እየመረመረ ነው። ከሩስያ ህግ የትኛውን እንደጣሰ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።
"ደህና፣ [ይሄ] ይከሰታል። አየር ላይ ሲሆን አንዳንዴ በስሜት መጓዝ ሊኖር ይችላል። ማቆምም አይቻልም። በእውነት አፍሬያለሁ" ሲል ክራሶቭስኪ ሰኞ ዕለት ይቅርታ ጠይቋል።
ክራስቭስኪ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ መብቶችን በመጠበቅ እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናትላይ ያነጣጠሩ የተመሳሳይ ጾታ መረጃዎችን የሚከለክለውን የሩሲያ ህግ በመተቸት ነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ያተረፈው። የሕጉ ደጋፊዎች “የተመሳሳይ ጾታ ፕሮፓጋንዳን” እየተዋጋን ነው ይላሉ።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ክራሶቭስኪ በአርቲ ላይ የሩስያ ቋንቋ ዳይሬክተር ሆኖ በማገልገል ላይ ነበር። የዩክሬንን ወረራ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን በመደገፉ በአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ተጥሎበታል።
መቀመጫውን ለንደን ያደረገው ታዋቂው ፀረ-ክሬምሊን ማህበረሰብ አንቂው ሚካሂል ክሆዶርኮቭስኪ በአርቲ አቋም ላይ ያለውን ትችት ገልጿል። "ማርጋሪታ ሲሞንያን የዩክሬን ልጆች እንዲገደሉ ከጠየቀው አንቶን ክራሶቭስኪ ጋር መተባበር አትፈልግም። በተቃራኒው የዩክሬን ልጆችን ከሚገድለው ፑቲን ጋር ግን ትተባበራለች” ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።
የቢቢሲ የምስራቅ አውሮፓ ጋዜጠኛ ሳራ ራይንስፎርድ በትዊተር ገጿ እንዳሰፈረችው ወደ ዩክሬን የሚወረወሩ የጥላቻ ንግግሮች በሩሲያ መንግስት ቲቪ ተለምደዋል። ክራሶቭስኪም ከብዙዎች አንዱ ነው ብላለች።