አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ሜክሲኮ እንዳይጓዙ ማሳሰቢያ ሰጠች

ታትሟል

የአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ባለስልጣናት በጸደይ ወራት ለእረፍት ብለው ዜጎች ወደ ሜክሲኮ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳሰቡ።

የቴክሳስ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ በእጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች መካከል ያለው ግጭት የሜክሲኮን ድንበር ለሚሻገር በሙሉ የደኅንነት አደጋን ይደቅናል ብሏል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ማስጠንቀቂያ የተሰማው ከቀናት በፊት አራት አሜሪካውያን የሜክሲኮን ድንበር እንደተሻገሩ በጠራራ ጸሐይ በእጽ አዋዋሪ ቡድን ከታገቱ በኋላ ነው።

ከታገቱት አራት አሜሪካውያን ሁለቱ ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለቱ ጎዳት ሳይደርስባቸው ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል።

“በአሁኑ ወቅት የእጽ አዋዋሪ ቡድኖች ግጭት እና ሌላ የወንጀል ድርጊት የሜክሲኮን ድንበር በሚሻገር የትኛውም ሰው ላይ ከፍተኛ የደኅንነት አደጋን ይደቅናል” ብለዋል የቴክሳስ የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ዳይሬክተር ስቲቭ ማክሮው።

ዳይሬክተሩ በአሁኑ ወቅት በሜክሲኮ እየተመለከትን ካለው የእጽ አዋዋሪ ቡድኖች እንቅስቃሴ እና ግጭት በመነሳት ማንም ሰው ወደ ሜክሲኮ ጉዞ እንዳያደርግ እናሳስባለን ብለዋል።

አራቱ አሜሪካዊያን ባለፈው ሳምንት ታግተው የነበረው ከቴክሳስ ግዛት ተሻግራ ወደ ምትገኝ ማታሞሮስ ከተማ እያሽከረከሩ ወደ ሜክሲኮ በመጓዝ ላይ ሳሉ ነበር።

አራቱ አሜሪካዊያን ወደ ሜክሲኮ አቅንተው የነበረው ለውበት ቀዶ ጥገና እንደነበረ ተዘግቧል። መሣሪያ ተደግኖባቸው ሲታገቱ በአንድ ክፍት የጭነት መኪና ላይ ታስረው ሲጫኑ አንድ ተንቀሳቃሽ ምሥል አሳይቷል።

እገታው ሲፈጸም በቅርብ ርቀት የነበረች አንዲት የ33 ዓመት ሜክሲኳዊት በአጋቾቹ በተተኩሰ ጥይት ሕይወቷ አልፏል።

ከክስተቱ በኋላ እገታውን ፈጽሟል የተባለው ስኮርፒኖስ የተባለው እፅ አዘዋዋሪ ቡድን አራት አሜሪካዊያንን አፍኖ ሁለቱን በመግደሉ ይቅርታ ጠይቆ ገዳይ ናቸው ያላቸውን አባላቱን የይቅርታ ደብዳቤ አስይዞ አሳልፎ ሰጥቷል።

ቡድኑ በጻፈው የይቅርታ ደብዳቤ ለማታሞሮስ ነዋሪዎች፣ ለተገደሉት አሜሪካዊያን ቤተሰቦች፣ አሜሪካዊያን ሲታገቱ በተባራሪ ጥይት ለተገደለች ሜክሲካዊት ይቅርታ ጠይቋል።

እጽ አዘዋዋሪ ቡድኑ “ለተፈጠረው ክስተት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂ ናቸው ያልናቸውን ሰዎች አሳልፈን ሰጥተናል” ካለ በኋላ ተላልፈው የተሰጡት አምስቱ የቡድኑ አባላት “ዲሲፒሊን በጎደለው ሁኔታ በራሳቸው ውሳኔ አሳልፈዋል” ብሏል።

የአሜሪካውያኑ በሜክሲኮ መታገት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያሻከረ ሆኗል።

የሪፓብሊካን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ወደ ሜክሲኮ ድንበር ጦር አሰማርቶ እጽ አዋዋሪ ቡድኖችን እንዲዋጋ ጠይቀዋል።

የሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኔኡል ሎፔዝ አብራዶር ግን የምክር ቤት አባሉን ምክረ ሃሳብ “በእብሪት የተሞላ” ሲሉ ገልጸውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት እህትማማቾች እና ጓደኛቸው ያገለገሉ እቃዎች በሚሸጡበት ገበያ ልብስ ለመሸጥ ከአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ወደ ሜክሲኮ ከተሻገሩ በኋላ የገቡበት እንዳልታወቀ የአሜሪካ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

ከጠፉት ሴቶች መካከል የአንዷ የትዳር አጋር ባለቤቱን ማግኘት አለመቻሉን ለፖሊስ ሪፖርት አድርጓል።

የድንበር ከተማ የሆነችው ፔኒታስ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሮኤል ቤርሜአ ወደ ሜክሲኮ ድንበር የተሻገሩት ሦስቱ ግለሰቦች ያሉበት እንደማይታቅ እና ጉዳዩን ኤፍቢአይ እንዲያውቀው መደረጉን ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።