ዜለንስኪ የኦዴሳውን ወደብ ጥቃት 'አረመኔያዊ' ሲሉ ሩሲያን ወቀሱ

የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ሩሲያ በኦዴሳ ወደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት ‘አረመኔያዊ’ ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ከሰዋል።

የዩክሬይንን የእህል ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ከተደረሰ ከሰዓታት በኋላ ነው ጥቃቱ የተሰነዘረው። ይህንንም ተከትሎ ስምምነቱ ላይሳካ ይችላል የሚል ስጋትም አንዣቧል።

ሞስኮ በጥቃቱ ዙሪያ የተናገረችው ነገር የለም። ጥቃቱ ቢሰነዘርም ኪዬቭ ለገበያ የሚቀርበውን እህል ለመላክ ዝግጅቷን እንደቀጠለች ነው።

ጥቃቱ ሞስኮ ስምምነቱን ስለማክበሯ እንደማትታመን ያሳያል ብለዋል ፕሬዚዳንት ዜለንስኪ።

ተመሳሳይ የሚሳኤሎች ጥቃቶችን መመከት የሚያስችል የአየር መከላከያ ዘዴዎችን ለማግኘት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

ዩክሬን ዋነኛ እህል ላኪ ሃገር ነች። በጦርነቱ ምክንያት ግን ወደ 20 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ እህል ለገበያ ሳይቀርብ በወደቦቿ ተከማችቶ ይገኛል።

አብዛኛው ከሩሲያ እና ከዩክሬን ስንዴ የሚያገኙት አፍሪካ ሃገራት የምግብ እጥረት እና የዋጋ ንረት ተፈጥሮባቸዋል።  አርብ በተደረገው ስምምነት መሠረት ሩሲያ የእህል ጭነት በሚጓጓዝበት ወቅት ወደቦችን ዒላማ እንደማታደርግ ተስማምታለች።

ስምምነቱ ከተፈረመ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሁለት የካሊቢር ሚሳኤሎች የኦዴሳ ወደብ ላይ መውደቃቸውን የዩክሬን ጦር ደቡባዊ ማዘዣ ማዕከል አስታውቋል። ሌሎች ሁለት ሚሳኤሎች በአየር መከላከያ ዘዴዎች ተመተው መውደቃቸውን አክሏል።

በጥቃቱ በወደቡ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም ሲል ማዕከሉ አስታውቋል።

ጥቃቱን ብዙዎች አውግዘውታል። የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ የዓለም የምግብ ቀውስን እያባባሰች ነው ሲሉ ከሰዋል።

ጥቃቱ ሩሲያ በስምምነቱ ላይ ባላት የቁርጠኝነት ተአማኒነት ላይ "ከባድ ጥርጣሬን ይፈጥራል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ሩሲያ ጥቃቷን ማቆም እና የተስማማችበትን የእህል ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አለባት" ብለዋል።

ክሬምሊን በጥቃቱ ላይ እስካሁን ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠችም። ስምምነቱ እንዲደረስ ያስቻለችው ቱርክ በሰጠችው መግለጫ የሩሲያ ባለስልጣናት የለንበትም ማለታቸውን ገልጻለች።

"ከሩሲያ ጋር ባደረግነው ግንኙነት ሩሲያውያን ከዚህ ጥቃት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው እና ጉዳዩን በቅርብ እና በዝርዝር እየመረመሩት መሆኑን ነግረውናል" ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሁሉሳይ አካር ተናግረዋል።

በሌላ ዜና የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ዩክሬን ሩሲያን ማሸነፍ እንደማትችል ተናግረዋል።

ሚንስትሩ በዓለም አቀፍ የወግ አጥባቂዎች ኮንፈረንስ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ጦርነቱ ሊቆም የሚችለው በዋሽንግተን እና በሞስኮ መካከል በሚደረግ የሠላም ድርድር ብቻ ነው ብለዋል።

"ጦርነቱን ለማሸነፍ ከመሞከር ይልቅ በሠላም ድርድር ላይ የሚያተኩር አዲስ ስልት ያስፈልጋል" ብለዋል ኦርባን። ጠቅላይ ሚንስትሩ በግጭቱ ላይ የነበራቸው አመለካከት ብዙውን ጊዜ ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ጋር የሚጋጭ ነው።

የኪዬቭ እና የሞስኮ ባለስልጣናት ከዩክሬን መውጫ ያጣው በሚሊዮን ቶን የሚቆጠረውን እህል ወደ ውጭ ለመላክ አርብ ከስምምነት ደርሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስምምነቱን “የተስፋ ብርሃን” የሰጠ ብሎ አወድሶታል።

ከስምምነቱ ለመድረስ ሁለት ወራትን ፈጅቷል።  ለ 120 ቀናትም የሚቆይ ሲሆን የማስተባበሪያ እና የክትትል ማዕከል በኢስታንቡል ይቋቋማል። ባለሙያዎችን ከበተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ቱርክ ፣ ሩሲያ እና ዩክሬን ባለስልጣናት ይመደብለታል። ሁለቱም ወገኖች ከተስማሙ ስምመነቱ ሊራዘምም ይችላል። 

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በኦዴሳ የተፈፀመው ጥቃት ሩሲያ ለዓለም አቀፍ ህግ ችላ ማለቷን ያሳያል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጥቃቱን በማያሻማ መልኩ አውግዘዋል። የእህል ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።