የጋና ፖሊስ የሃይማኖት ሰባኪያን ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ትንቢቶችን እንዳይናገሩ ከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጋና ፖሊስ የሃይማኖት መሪዎች አዲስ ዓመትን በማስመልከት በሕዝቡ ውስጥ ፍርሃት፣ ጭንቀት ወይም ሞትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ትንቢቶችን እንዳይናገሩ አስጠነቀቀ።
ከቀናት በኋላ ከሚጀመረው የአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት ቀደም ብሎ ፖሊስ እንዳስጠነቀቀው፣ የእምነት ነጻነት የሌሎችን መብት የሚጥስ መሆን የለበትም ብሏል።
ጋና ውስጥ የሃይማኖት መሪዎች በአዲስ ዓመት ወቅት የተለያዩ አይነት ትንቢቶችን ለተከታዮቻቸው መንገር የተለመደ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት የሚነገሩ የአዲስ ዓመት ትንቢቶች በሕዝቡ ላይ ጭንቀትን ያስከትላሉ ብሏል።
የፖሊስን ማስጠንቀቂያ የተቃወሙ ሰዎች በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጥበቃ የሚደረግለትን የእምነት ነጻነትን የሚቃረን በመሆኑ ሕገ ወጥ ነው ሲሉ ተችተውታል።
ጋና ውስጥ አዲስ ዓመት ሲቃረብ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን ፓስተሮች የሚያውጁትን የአዲስ ዘመን ትንቢት ለመስማት በአብያተ ክርስቲያናት ይታደማሉ።
በሃይማኖት መሪዎቹ የሚነገሩት ትንቢቶችም በአብዛኛው መልካም ተስፋን የሚያጭሩ እና መጥፎ ነገሮች እንደሚገጥሙ የሚናገሩ ናቸው።
ይህ የፖሊስ ትዕዛዝ የወጣው ባለፈው ዓመት ሞት እና መቅሰፍት እንደሚከሰት የሚገልጽ ትንቢት በሕዝቡ ውስጥ ከባድ ጭንቀትን ከፈጠረ በኋላ መሆኑን አንድ የጋና ድረ ገጽ ዘግቧል።
ፖሊስ አሁን ባወጣው መግለጫ የሃይማኖት ተቋማት “ትንቢቶችን በሕግ ተቀባይነት ባላቸው መንገዶች” በመግለጽ እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል።
ነገር ግን ጋናዊው ጠበቃ ሳሚ ዳርኮ ፖሊስ የሰጠውን ትዕዛዝ “ሕገ ወጥ ነው” ሲሉ ተቃውመውታል።
ማስጠንቀቂያው “በአገሪቱ ፍርድ ቤት ለክርክርም ሆነ ለትርጉም ብቁ አይደለም።በጋና ውስጥ ፖሊስ ትንቢቶችን እንዲቆጣጠር ምንም አይነት ሕጋዊ ሥልጣን አልተሰጠውም” ሲሉ ጠበቃው ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም “ሃይማኖት ነጻነት በእምነት ስፍራዎች ‘አምልኮት ከመፈጸም ነጻነት’ የበለጠ ነው። ስለዚህም ሰዎች ተለይቶ የተገለጸ ሕግን እስካልጣሱ ድረስ ከባህልና ከመንግሥት ፍላጎት ጋር ለማጣጣም ሲሉ የእምነታቸው ሕግጋት መጻረር የለባቸውም” ብለዋል።
ፖሊስ እንዳለው አዲስ ዓመት ከመግባቱ አራት ቀናት በፊት ያለው ዕለት የሃይማኖት ተቋማት ትንቢትን በሚመለከት ስለሚያስተላልፉት መልዕክት መረጃዎችን የሚሰጡበት ቀን ነው።
“በዚህ ዕለት ሁላችንም ሃይማኖታዊ ሥርዓታችንን ስንከውን በሕግ ጥላ ሥር ደኅንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ፣ በአስተማማኝ ስፍራ፣ ጉዳት፣ አደጋ ወይም ሞት እንደሚከሰት የሚገልጹ ትንቢቶች ከሚያስከትሉት ጭንቀት ነጻ በሆነ ሁኔታ መሆን አለበት” ሲል የፖሊስ መግለጫ አሳስቧል።












