ዩናይትድ ለአንቶኒ ከ80 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ለመክፈል ተስማማ

ታትሟል

ማንቸስተር ዩናይትድ ብራዚላዊውን አማካይ አንቶኒን ለማስፈርም ከአያክስ ጋር ተስማማ።

ዩናይትድ ለተጫዋቹ 80.75 ሚሊዮን ፓውንድ ለመክፈል የተስማማ ሲሆን እንደ ሁኔታው እየታየ የሚጨመር 4.25 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚከፍልም ይጠበቃል።

የ22 ዓመቱ ተጫዋች የሕክምና ምርመራውን ለማጠናቀቅ በሚቀጥሉት 48 ሰዓታት ማንቸስተር ከተማ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ዝውውሩ ከተሳካ አንቶኒ ከሃሪ ማጓየር እኩል የክለቡ ሁለተኛው ውዱ ተጫዋች ይሆናል። 89 ሚሊዮን ፓውንድ የተከፈለበት ፖል ፖግባ የክለቡ ውድ ተጫዋች ነው።

አንቶኒ ለአያክስ 82 ጊዜ ተሰልፎ 25 ጎሎችን ሲያስቆጥር 22 ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል። ብራዚላዊው እአአ በ2020 ነበር ከብራዚሉ ሳኦ ፓውሎ ወደ ሆላንዱ ክለብ በማቅናት ከአሁኑ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ጋር መሥራት የጀመረው።

አንቶኒ እአአ በ2021 ለብራዚል ብሔራዊ ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰለፈ ሲሆን በዘጠኝ ጨዋታዎች 2 ጎሎችን አስቆጥሯል።

አንቶኒ በእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ አራተኛው ውዱ ተጫዋች በመሆን ደረጃውን ይጋራል። ተጫዋቹ ግራ እግር ተጫዋች ሲሆን በቀኝ ክንፍ በኩል ይሰለፋል።

ፖግባ ወደ ዩናይትድ፣ ሮሜሉ ሉካኩ ወደ ቼልሲ፣ ጃክ ግሪሊሽ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ያደረጉት ዝውውር ቀዳሚዎቹን ሦስት ስፍራዎች ይይዛሉ።  

ዩናይትድ በመጪው ሐሙስ ወደ ሌስተር በማቅናት የአምስተኛ ሳምንት ጨዋታውን ያከናውናል። አንቶኒ ለዚህ ጨዋታ ለመድረስ ህክምናውን ማጠናቀቅ እና የስራ ፍቃዱን ማግኘት ይጠበቅበታል።

ተጫዋቹ በዚህ የዝውውር መስኮት አምስተኛው የቡድኑ ፈራሚ ይሆናል። ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ፣ ካሴሚሮ፣ ታይሬል ማላሲያ እና ክርስቲያን ኤሪክሰን ቀድመውት ኦልድ ትራፎርድ ደርሰዋል።

ክርስቲያኖ ሮናልዶ በክለቡ መቆየቱ አሁንም ውሉ ያለየለት ጉዳይ ሆኗል። የ37 ዓመቱ ኮከብ ክለቡን ልለቀቅ ብሎዋል መባሉ የቡድኑን መንፈስ እየጎዳው መሆኑ ይገለጻል።