ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩኬ በአንዳንድ ስደተኞች ላይ የኤሌክትሮኒክስ መለያ ልትገጥም ነው
በአነስተኛ ጀልባዎች ወይም በጭነት መኪኖች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገቡ አንዳንድ ጥገኝነት ጠያቁዎች የኤሌክትሮኒክስ መለያ ሊገጠምላቸው መሆኑ ተገልጿል።
የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ሙከራ አካል ነው የተባለው እርምጃ መንግሥት አደገኛ ወይም አላስፈላጊ በሚላቸው መንገዶች የገቡና የሚባረሩ ስደተኞችም ላይ ለ12 ወራት ያህል እንደሚተገበር ተገልጿል።
ቦሪስ ጆንሰን “ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደተቀረው የአገሪቱ ክፍል መጥፋት እንደማይችሉ ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው" ብለዋል።
ተቺዎች በበኩላቸው ይህ እቅድ ስደተኞችን እንደ ወንጀለኞች የሚመለከት ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ይህ ጅማሮ ከእንግሊዝ ወደ ሩዋንዳ ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለማጓጓዝ ሊደረግ የነበረው የመጀመሪያው በረራ በአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት የመጨረሻ ደቂቃ ጣልቃ ገብነት ከተሰረዘ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።
የመጀመሪያው የኤሌክትሮኒክ መለያ የሚገጠምላቸው ያንን በረራ በተሳካ ሁኔታ እንዳይሳካ የተሟገቱ የሆኑ ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ።
የሃገር ውስጥ ጽሕፈት ቤት በእንግሊዝ እና በዌልስ የጀመረው የኤሌክትሮነክስ መለያ መግጠም ጥገኝነት ጠያቂዎች ሂደታቸው በብቃት እንዲከናወን ሊረዳ ይችላል ወይ የሚለውንም እንደሚፈትሽ አስታውቋል።
ምንም እንኳን ሙከራው የተጀመረ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር እስካሁን የኤሌክትሮኒክስ መለያ ተገጥሟል ስለሚለው ምንም አይነት አስተያየት አልሰጠም ።
መለያ የተገጠመላቸው ስደተኞች የሰዓት እላፊ ገደብ ሊጣልባቸው ይችላል እንዲሁም የተሰጧቸውን ትዕዛዞች የማያከብሩ ከሆነም ወደ እስር ቤት ሊወሰዱ ወይም ሊከሰሱ ይችላሉ።
መመሪያው ከዩናይትድ ኪንግደም እንደሚባረሩ የተነገራቸው ስደተኞች ሊሸሹ ይችላሉ እንዲሁም የኢሚግሬሽን የዋስትና ሁኔታዎችን ላያከብሩ እንደሚችሉም አትቷል።
ከስደተኞች ጋር የሚሰሩ ሰራተኞች መሳሪያው በሰውዬው አእምሮአዊ ወይም አካላዊ ጤንነት ላይ ከባድ ጉዳት ያደርስ እንደሆነ ወይም የስቃይ ወይም የዘመናዊ ባርነት ሰለባ መሆን አለመሆኑን ማጤን አለባቸው።
የሆም ኦፊስ መመሪያ ህጻናትን ወይም እርጉዝ ሴቶችን አይጨምርም ይላል።