ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የትዊተር ተጠቃሚዎች ያልተመለደ ችግር ገጥሞናል አሉ
በዓለም አቀፍ ደረጃ አንዳንድ የትዊተር ተጠቃሚዎች መልእክት ማሰራጨት እንደተቸገሩ ተናገሩ።
ትዊተር ኩባንያ በበኩሉ ድረ ገጹ መጠነኛ መንገጫገጭ ገጥሞት ስለነበረ ነው ችግሩ የተከሰተው ብሏል።
ተጠቃሚዎች አዲስ መልእክት በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ለመጻፍ ሲሞክሩ “ለቀኑ የተቀመጠልዎትን ገደብ አልፈዋል” የሚል መልእክት ይደርሳቸዋል።
የትዊተር ባለቤት ቢሊየነሩ ኤሎን መስክ ኩባንያውን በ44 ቢሊዮን ዶላር ከገዛ በኋላ ወጪ ቁጠባ በሚል ከወራት በፊት በሺህ የሚቆጠሩ ሠራኞችን ማባረሩ አይዘነጋም።
ትዊተር በኤሎን መስክ እጅ ከመውደቁ በፊት የሠራተኞቹ ብዛት 8ሺህ የነበረ ሲሆን አሁን 2ሺህ ገደማ ሠራተኞች ናቸው ያሉት።
ባለሙያዎች ቀደም ብለው ኤሎን መስክ ይህን ሁሉ ሠራተኛ በአንድ ጊዜ ከቀነሱ በኋላ የከፋ ቴክኒክ ችግር በትዊተር ላይ ሊደርስ እንደሚችል ገምተው ነበር።
ይሁንና አሁን የተከሰተው ችግር ከሠራተኛ ቅነሳ ጋር በተያያዘ የመጣ ይሁን ወይም በሌላ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።
አሁን እየወጡ ባሉ መረጃዎች ትናንት ረቡዕ የተከሰተው ይህ ቴክኒካዊ ችግር በብዛት ዛሬ ተቀርፎ እንደታየ ተዘግቧል።
ችግሩ ገጠመን ያሉ ተጠቃሚዎች እንደሚሉት ምንም እንኳ አንድ መልእክት ራሱ በዕለቱ (ትናንት) ሳይለጥፉ ቢቀሩም ኩባንያው ግን “በቀን የተፈቀደልዎን 2ሺህ 400 ትዊት ገደብ አልፈዋል” የሚል መልእክት ይልክላቸው እንደነበር አብራርተዋል።
በዚህ ትዊተር ላይ በተፈጠረው ጊዝያዊ ችግር በዓለም ደረጃ ምን ያህል ተጠቃሚዎች እንደታወኩ ለጊዜው አልታወቀም።
ትዊተር የችግሩን መፈጠር አምኖ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራሁ ነው ብሏል።
ከዚህ ችግር ሌላ የትዊተር ተጠቃሚዎች ተመሳሳይ ሌሎች ችግሮች እየገጠሟቸው እንደሆነ ሲናገሩ ነበር።
ለምሳሌ አንዳንዶቹን “ትዊተራችሁን ከዘጋችሁት በርካታ ተጠቃሚዎች ዘንድ መድረስ ትችላላችሁ’ የሚል መልእክት ሲደርሳቸው ነበር።
በቴክኖሎጂ ዜና ዘገባ የሚታወቀው ‘ዘ ኢንፎርሜሽን’ የተሰኘ ሚዲያ በቅርቡ ኤሎን መስክ ሠራተኞቹ ለትዊተር አዲስ ገጽታ ለመስጠት ፈጠራቸውን ገታ እንዲያደርጉ እንዳዘዘ ዘግበዋል።
ይህ መመሪያ የተላለፈው አዲስ ገጽታ ከመፍጠር በፊት መጀመርያ የትዊተርን አገልግሎት አሰጣጥ አስተማማኝነት ለማጎናጸፍ እንደሆነ ይገመታል።
ትዊተር በወር 8 ዶላር ኪራይ ለሚከፈሉ የአሜሪካ ደንበኞቹ ዘለግ ያለ መልእክት መጻፍ እንዲችሉ ይፈቅዳል።
የትዊተር “የሰማያዊ ጭረት” ባለቤቶች በወር 8 ዶላር ኪራይ ስለሚከፍሉ የመልእክታቸው ርዝመት እስከ 4ሺህ ሆሄያት ሊዘልቅ ይችላል።
ሌላው ሰፊው የነጻ አገልግሎት ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ግን በአንድ ጊዜ በሰሌዳው ሊለጥፍ የሚችለው 240 ሆሄያትን የያዘ መልእክት ብቻ ነው።
ይህ በእንዲህ ሳለ እንደ ትዊተር ሁሉ ዩትዩብም ወደ 65ሺህ ተጠቃሚዎቹ ቴክኒካዊ ችግር እንደገጠማቸው ተሰምቷል።
ዩትዩብን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የጉጉል እህት ኩባንያ ‘አልፋቤት’ ችግሩን እየፈተሽኩ እገኛለሁ ብሏል።
“እናዝናለን ለተፈጠረው ነገር፤ ምን እንደተፈጠረ እየፈተሽን ነው ታገሱን" ብሏል የዩትዩብ አስተዳዳሪ ኩባንያ አልፋቤት።