በአሜሪካ የበረዶ ውሽንፍር እያስከተለ ያለው ሞት መጨመሩ ተነገረ

የበረዶ ውሽንፍር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በሰሜን አሜሪካ የተከሰተው ከባድ የበረዶ ውሽንፍር የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ መሆኑን የኒውዮርክ ግዛት ባለስልጣናት ተናገሩ።

ኤሪ በተባለና ቡፋሎ ከተማን በሚያጠቃልለው አከባቢ ከበረዶ ውሽንፍር ጋር በተያያዘ ቢያንስ 34 ሰዎች መሞታቸውን የአከባቢው ባለስልጣን ማርክ ፖሎካርዝ ትናንት ገልጸዋል።

ባለስልጣናት የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሶስት ሰዎችን ማንነት ለመለየት እያደረጉ ያለውን ጥረት ቀጥለዋል።

የፈረንጆቹ ገናን ተከትሎ ባሉት የእረፍት ቀናት በበረዶ ውሽንፍር ምክንያት በስምንት ግዛቶች ቢያንስ 60 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1977 በቡፋሎ ግዛት በተከሰተው እና በአስከፊነቱ ከሚታወቀው የበርዶ ውሽንፍር ካስከተለው የሞት ቁጥር በላይ በኤሪ ግዛት ባለፉት ጥቂት ቀናት የተመዘገበው ልቆ ተገኝቷል።

29 ሰዎች በበርዶ ውሽንፍር ምክንያት መሞታቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ የአየር ንብረት አገልግሎት ያወጣው መረጃ አመላክቷል።

ማርክ ፖሎካርዝ  ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “እጀግ በርካታ ሰዎች የሞቱበት አስከፊ የበረዶ ውሽንፍር ነው’ ብለዋል።

ሆኖም ኒውዮርክን ጨምሮ የአየር ጸባዩ ከፍቶ በነበረባቸው አካባቢዎች ሁኔታዎች መሻሻል ጀምረዋል።

በኤሪ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠባቸው ሰዎች ከ1 ሺህ ያነሱ መሆናቸውን እና 95 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች መግለጫውን የሰጡበት ቀን ከመጠናቀቁ በፊት የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በበረዶ ውሽንፍር ክፉኛ ተመታ የነበረችው የቡፋሎ ከተማ መንገዶችም መሻሻል እያሳዩ ነው።

65 በመቶ የሚሆኑት የከተማው መንገዶች ለመንገደኞች ቢያንስ አንድ መተላለፊያ ቢፈቀድም ባለው ከባድ ሁኔታ ምክንያት መኪና ማሽከርከር አሁንም እንደተከለከለ መሆኑን ሃላፊው ተናግረዋል።

ባለፈው አርብ ተዘግቶ የነበረው እና በዕለቱ ሁሉም በረራዎች ተዘግተውበት ወይም ዘግይተውበት የነበረው የቡፋሎ ከተማ አየር ማረፊያም ደግም ስራ ጀምሯል።

የከተማዋ የባቡር አገልግሎት በውስን ሁኔታ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በሌሎች የአሜሪካ እና የካናዳ አከባቢዎችም ከባዱ የክረምት አየር ሰዎችን ለሞት እያደረገ የእለተ እለት እንቅሰቃሴን እጅግ እያስተጓጎለ ነው።

በዋሽንግተን እና በኦሪገን ከማክሰኞ ከሰዓት ጀምሮ ከ70 ሺህ በላይ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደተቋረጠባቸው የኤሌክትሪክ አገልግሎን የሚከታተል አንድ ድረገጽ አመላክቷል።