የ17 ዓመቷ ሚስቱን አንገት ቀልቶ የገደለው ኢራናዊ የስምንት ዓመት እስር ተፈረደበት

ታትሟል

በኢራን የ17 ዓመት ዕድሜ ያላትን ሚስቱን አንገት ቀልቶ የገደለው ግለሰብ የስምንት ዓመት እስር እንደተፈረደበት።

ባለፈው ዓመት በኢራን ሀቫስ በተባለው ስፍራ ሳጃድ ሃያዳሪ የተባለው ግለሰብ “የክብር ግድያ” ሲል የጠራውን ድርጊት ከፈጸመ በኋላ የባለቤቱን የተቆረጠ አንገት ይዞ ሲንቀሳቀስ የሚያሳዩ ምሥሎች መውጣታቸው ተከትሎ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

የየአገሪቱ የፍትሕ መሥሪያ ቤት ቃል አቃባይ ገዳዩ ላይ የስምንት ዓመት እስራት ሊፈረድበት የቻለው የሞና ቤተሰቦች ከብቀላ ይልቅ ይቅርታ ስለመረጡ ነው ብለዋል።

ቀደም ብሎ የሟች አባት ለግድያው ፍቃዳቸውን እንዳልሰጡ ገልጸው ነበር።

ሞና ትዳር የመሠረተችው የ12 ዓመት ልጅ ሳለች ሲሆን በ14ኛ ዓመቷ ልጅ ወልዳ ነበር።

ሟች ፍቺ ብትጠይቅም ባለቤቷ ሳይቀበለው በመቅረቱ እና በቤት ውስጥ ይፈጽምባታል የተባለው ጥቃት በመሸሽ ወደ ቱርክ ተሰዳ እንደነበር የኢራን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሆኖም ግድያው ከመፈጸሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ባለፈው ዓመት ቤተሰቦቿ ምንም እንደማይደርስባት ማረጋገጫ ከሰጧት በኋላ ወደ አገሯ ተመልሳለች።

ቃል አቀባዩ ማሱድ ስታይሺ ባለቤቷ በግድያው ሰባት ዓመት ከስድስት ወር ሲፈረድበት ለጥቃቱ ደግሞ ተጨማሪ ስምንት ወራት እንደተቀጣ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

ጨምረው ብይኑ በኢራን ሕግ መሠረት የተሰጠ መሆኑን ጠቀሰዋል። የሟች ቤተሰቦች ይቅርታ ካላደረጉ በስተቀር በኢራን ሆን ብሎ የሰው ነፍስ ያጠፋ ሰው በሞት እንዲቀጣ ሕጉ ያዛል።

የገዳይ ወንድም ለግድያው ተባባሪ በመሆን የ45 ወራት እስራት ተፈርዶበታል።

ይህ አሰቃቂ ግድያ በኢራን ሴቶችን ከቤት ውስጥ ጥቃት የሚጠብቅ እና የሚከላከል አዲስ ሕግ ይውጣ የሚል ጥያቄ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

በተጨማሪም በሕግ የተቀመጠው ዝቅተኛ የጋብቻ ዕድሜ ከፍ ይበል የሚል ጥያቄም አሰነስቶ ነበር።

ሕጉ 13 ዓመት የሞላት ሴት እንድታገባ የሚፈቅድ ሲሆን የቤተሰቦቿ ፍቃድ ከሆነ በሕግ አማካሪዎች ታይቶ ከዚያም በታች ዕድሜ ያላት ሴት ልትዳር ትችላለች።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2020 ከእጮኛዋ ሸሽታ አምልጣለች የተባለችው የ14 ዓመት ልጅ አባቷ አንገቷን ቀልተው መግደላቸውን ተከትሎ ተመሳሳይ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።

አባት ልጃቸውን ከመግደላቸው በፊት ድርጊቱን ቢፈጽሙ ምን ዓይነት ቅጣት ሊጠብቃቻው እንደሚችል ጠበቃ አማክረው ነበር።

በኋላም በሕጉ ከተቀመጠው ከፍተኛ ቅጣት አንድ ዓመት ዝቅ ብሎ የዘጠኝ ዓመት እስር ተፈርዶባቸል።

መንግሥት ሴቶች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን ወንጀል የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ አጽድቋል።

ሆኖም ገና ወደ ፓርላማ ያልተላለፈ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ባለሙያዎች በበቂ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

ከወራት በፊት አንዲት ሴት ሂጃቧን “በአግባቡ አለበሰችም” በሚል በሞራል ደንብ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ መሞቶን ተከትሎ ኢራን አሁን ላይ በጸረ መንግሥት ተቃውሞ እየተናጠች ትገኛለች።

እስካሁን አራት ሰዎች ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ የተገደሉ ሲሆን ሌሎች 18 ሰዎች ደግሞ በሞት እንዲቀጡ ተበይኖባቸዋል።

ይህ ፍርድ የተሰጠው በአሳፋሪ መንገድ በተካሄደ ችሎት ነው ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች ገልጸዋል።