ታሊባን አሜሪካዊውን ታጋች ሲፈታ አሜሪካ ከታሊባን ጋር ግንኙነት ያለው የአፍጋኒስታን መሪ ለቀቀች

ታትሟል

ታሊባን እአአ ከ2020 ጀምሮ ታግቶ የነበረውን የአሜሪካዊ መሐንዲስ ሲለቅ አሜሪካ በበኩሏ ከ2005 ጀምሮ በሃገሯ አስራ ያቆየችውን የአፍጋኒስታን የጎሳ መሪ በልዋጭ ለቃለች።

ማርክ ፍሬሪክስ ሰኞ ዕለት በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ተላልፎ መሰጠቱን ታሊባን ተናግሯል።

በምላሹም በአደንዛዥ ዕፅ አዘዋዋሪነት የዕድሜ ልክ እስራት እስራት የተላለፈበትን ባሽር ኑርዛይ የተባለ የታሊባን አጋርን ተቀብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እንደተናገሩት ልውውጡ በቀላል የማይታዩ “አስቸጋሪ ውሳኔዎች” ያስፈለጉት ነበር ብለዋል።

የ60 ዓመቱ ፍሬሪክስ በታሊባን ታፍነው የተወሰዱት በምዕራባውያን የሚደገፈው መንግስት ወድቆ ቡድኑ ወደ ስልጣን ከመመለሱ ከአንድ አመት በፊት ነው።

ካቡል ውስጥ በሲቪል መሐንዲስነት ለ10 ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል። የፍሬሪክስ እህት የሆነችው ቻርሊን ካኮራ ቤተሰቡ በመመለሱ ጉዳይ ተስፋ ቆርጦ እንደማያውቅ ተናግራለች።

"ወንድሜ በደህና ወደ ቤት እየመጣ መሆኑን በመስማቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከታገተ ጀምሮ ቤተሰባችን ከ31 ወራት በላይ በየቀኑ እዚህ ለመድረስ ፀሎት አድርጓል” ብላለች በመግለጫዋ። 

" ማርክን ወደ ቤት ባመጣው ስምምነት ላይ አንዳንድ ሰዎች ሲከራከሩ ነበር። ነገር ግን ፕሬዝዳንት ባይደን ትክክል የሆነውን አድርገዋል። የንፁህ አሜሪካዊ አርበኛ ህይወትን አዳኑ።” በማለት መግለጫዋ ላይ ሰፍሯል።

የፍሬሪክስ አባት አርት ፍሬሪክስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከባይደን ጋር በስልክ ቢነጋገሩም እስካሁን ማርክን ማነጋገር አለመቻላቸውን አስታውቀዋል።

"እፎይታ ተሰምቶናል። በጣም ረዥም ጊዜ አልፏል" ብለዋል።

የቀድሞው የባህር ኃይል መኮንን መታፈን በአሜሪካ እና በታሊባን መካከል ያለውን ግንኙነት ላለማሻሻሉ ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። አሜሪካ እስካሁን ለታሊባን አስተዳደር እውቅና አልሰጠችም። 

ፕሬዝዳንት ባይደን በጥር ወር “ታሊባን ለህጋዊነት ያለውን ምኞት ግምት ውስጥ በማስገባት ማርክን በፍጥነት መልቀቅ አለበት። ይህ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም” ብለዋል ።

ቢያንስ አንድ ሌላ አሜሪካዊ አሁንም በታሊባን እጅ ይገኛል። ፊልም ሰሪው ኢቮር ሺረር እና አፍጋኒስታናዊው አዘጋጅ ፋይዙላህ ፋይዝባኽሽ በነሐሴ ወር ነበር በካቡል ውስጥ የታሰሩት።

የፍሬሪክስ ቤተሰብን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠራው የቀድሞ የብሄራዊ ደህንነት ባልደረባው ኤሪክ ሊብሰን በበኩሉ ባይደን የፍሬሪክስን ለማስፈታት የወሰደው እርምጃ “ውጭ ሃገር ታግተው ወይም በግፍ ታስረው የሚገኙ ለሌሎች አሜሪካውያንም በአስቸኳይ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች ነው” ብሏል።

ሊብሰን አክሎም “የተያዙት አሜሪካውያን ስለሆኑ ነው። እናም የአሜሪካ መንግሥት ወደ ሃገራቸው እንዲያመጣቸው ይፈልጋሉ" ብሏል።

ባሽር ኑርዛይ አፍጋኒስታን መዲና ሲደርሱ የጀግና አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን የታሊባን ተዋጊዎች የአበባ ጉንጉን ይዘው ተቀብለዋቸዋል።

“እኔና አሜሪካዊው ነጻ መውጣታችን በሃገራቱ መካከል ሠላም ይፈጥራል” ሲሉ ም ተናግረዋል።

ኑርዛይ የታሊባን መስራች የሆኑት የሙላህ ኦማር የቅርብ አጋር እና ጓደኛ ነው። በ1990ዎቹ የመጀመሪያውን የታሊባን መንግሥትንም በገንዘብ ረድቷል።

ይፋዊ ስልጣን ባይዝም "ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ ጠንካራ ድጋፍ አድርጓል" ሲሉ የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ለኤኤፍፒ የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

ኑርዛይ በሄሮይን ኮንትሮባንድ ወንጀል 17 ዓመታትን በአሜሪካ እስር ቤት አሳልፏል። የታሊባን እምብርት በሆነው በደቡባዊ አፍጋኒስታን በሚገኘው በካንዳሃር ግዛት ውስጥ ሰፊ ኦፒየም እርሻ ላይ መሰማራቱን አቃቤ ህግ አሳውቋል።

እአአ በ 2005 በቁጥጥር ስር በዋለበት ጊዜ  በዓለም ላይ ካሉ ታላላቅ የአደንዛዥ ዕጽ አዘዋዋሪዎች አንዱ ተደርጎ ይቆጠር ነበር። አብዛኛውን የዓለም የአደንዛዥ ዕጽ ከሚይዘው የአፍጋኒስታን ገበያ ከግማሽ በላይ የሚሆነውንም ይይዛል።

እአአ በ 2008 በኒውዮርክ በሚገኝ ፍርድ ቤት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሄሮይን በድብቅ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለማዘዋወር በማሴር ተከሷል።