በአሜሪካ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ጠበቅ ያለ የመሳሪያ ህግ እንዲተገበር ለተቃውሞ ወጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ የተፈጸሙ ሁለት የጅምላ ግድያዎችን ተከትሎ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ነዋሪዎች ጠበቅ ያለ የጦር መሳሪያ አጠቃቀም ህግ እንዲተገበር ለተቃውሞ ወጡ።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰልፎች የሚል ስያሜ በተሰጠው በዚህ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ አብዛኛዎቹ እንዲተኮስብኝ አልፈልግም የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ነበር።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተቃውሞውን ደግፈው ኮንግረሱ “በጦር መሳሪያ አጠቃቀም ላይ የደህንነት ህግ እንዲያወጣ” ጠይቀዋል።
ምንም እንኳን የህግ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ተስፋ ቢደረግም በሌላ በኩል የጦር መሳሪያ የህግ ለውጥ በማይፈልጉ ሪፐብሊካኖች ሊቀለበስ ይችላል።
በባለፈው ወር በኡቫልዴ፣ ቴክሳስ በሚገኝ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተፈጸመ ጥቃት 19 ህፃናት እና ሁለት ጎልማሶች ተገድለዋል።
ከዚያ ቀደም ብሎ በቡፋሎ፣ ኒው ዮርክ 10 ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት በአሜሪካ ውስጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ላይ እርምጃ እንዲወስዱ በተደጋጋሚ ጥሪ የሚቀርብበት ምክንያት ሆኗል።
በአውሮፓውያኑ 2018 በፍሎሪዳ ፓርክላንድ ትምህርት ቤት ከተከሰተው ጥቃት በተረፉ ግለሰቦች የተቋቋመው “ገን ሴፍቲ ግሩፕ ማርች ፎር አወር ላይቭስ” የተሰኘ ድርጅት ሲሆን ይህንን ሰልፍ ያዘጋጀው በተጨማሪም ዋሽንግተን ዲሲ፣ ኒውዮርክ፣ ሎስ አንጀለስ እና ቺካጎን ጨምሮ 450 ሰልፎች እንደሚደረጉ ገልጿል።
ተቋሙ እንዳለው ዜጎች እየረገፉ ባለበት ሁኔታ ፖለቲከኞች ችላ ብለው አርፈው እንዲቀመጡ እንደማይፈቅድ ተናግሯል።
“ማርች ፎር አወር ላይቭስ” እንዳለው ) የፖለቲካ መሪዎች ቸልተኝነት አሜሪካውያንን እየገደለ ነው ብሏል።
የድርጅቱ የቦርድ አባል የሆኑት ትሬቨን ቦስሊ በመግለጫቸው " ሰዎች እየሞቱ ባሉበት ሁኔታ ፖለቲከኞች ዝም ብለው እንዲቀመጡ አንፈቅድም” ብለዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ ተቃዋሚዎችን ባነጋገሩበት ወቅት በፓርክላንድ ጥቃት ከተረፉት መካከል አንዱ ዴቪድ ሆግ በኡቫልዴ የተፈጸመው የህፃናት ግድያ “ቁጣ ሊያስነሳብን እንዲሁም ለለውጥ የምንሰራበት ነው። ማለቂያ በሌለው ክርክር መሞላት ሳይሆን የለውጥ ጥያቄዎች መነሳት አለበት” ብሏል።












