ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ያስተዋወቁት ክሪፕቶከረንሲ በአጭር ጊዜ በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍ አስገኘ
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የራሳቸውን ክሪፕቶከረንሲ አስተዋወቁ። በገበያው ላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ትርፍም እያስገኘም ነው።
ሰኞ ዋይት ሀውስ የሚገቡት ትራምፕ $Trump የተባለ ሚምኮይን ክሪፕቶከረንሲ አስተዋውቀዋል።
የትራምፕ ድርጅቶች አጋር በሆነው ሲአይሲ ዲጂታል አማካይነት ነው ትራምፕ ክሪፕቶከሪንሲውን ያስተዋወቁት።
ከዚህ ቀደም ትራምፕ ሽቶና ጫማ በስማቸው አምርተው ነበር።
ሚምኮይን የተበላው ክሪፕቶከረንሲ በበይነ መረብ ከፍተኛ ዕውቅና አለው። ተጨባጭ ዋጋ የሌለው እና አስጊ ቢሆንም የኢንቨስትመንት አማራጭ ናቸው።
የትራምፕ ሳንቲሞች ከተዋወቁ በኋላ ወደ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘታቸውን ኮይን ማርኬት ካፕ የተባለው ድረ ገጽ አስታውቋል።
ትራምፕ 'ፋይት ፋይት ፋይት' በሚል ስያሜ ደላዌር ውስጥ የከፈቱት ድርጅት 80% ድርሻ አለው።
ትራምፕ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያገኙ ግልጽ አይደለም።
"ይፋዊ ሚሜ ይፋ ተደርጓል። በማሸነፋችን መደሰት አለብን" ብለዋል ትራምፕ።
200 ሚሊዮን ዲጂታል ቶክን የተሠራ ሲሆን ተጨማሪ 800 ሚሊዮን የሚዘጋጅም ይሆናል።
"የትራምፕ ሚም የማይበገረው መሪ መታሰቢያ ነው" በሚል በድረ ገጻቸው ተጽፏል።
ሳንቲሙ እንደ ኢንቨስትመንት አማራጭ መወሰድ እንደሌለበትና ፖለቲካዊ ቅስቀሳ እንዳልሆነ ተገልጿል።
ትራምፕ በፕሬዝዳንትነታቸው እያተረፉ ነው ብለው ተቺዎቻቸው ይነቅፏቸዋል።
የክሪፕቶከረንሲ ኢንቨስትመንት ባለሙያ ኒክ ቶማንዮ "ትራምፕ 80 በመቶ ድርሻ ባለቤት ናቸው። ከበዓለ ሲመታቸው በፊት ብዙዎች ጋር ሊደርስ ይችላል" ይላል።
ሳንቲሞቹ ካላቸው ዋጋ የተጋነነ ዋጋ በመስጠት በበይነ መረብ መነጋገሪያ ሲሆኑ ይስተዋላል።
የክሪፕቶከረንሲ ኢንቨስትሮች በበኩላቸው በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ገበያው እንደሚያድግ ተስፋ አላቸው።
የጆ ባይደን አስተዳደር ክሪፕቶከረንሲ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር ውስጥ ከማስገባትና ከማጭበርበር ጋር በተያያዘ ጥቅም ላይ መዋሉን ይተች ነበር።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም እምብዛም ክሪፕቶከረንሲን አይቀበሉም ነበር። ሆኖም ግን አምና በናሽቪል በተካሄደ የቢትኮይን ውይይት ላይ ተገኝተው አሜሪካ "የዓለም የክሪፕቶ መዲና ትሆናለች" ብለዋል።
ልጆቻቸው ኤሪክና ዶናልድ ጁንየርም በክሪፕቶከረንሲ ኢንቨሰት ያደርጋሉ።