ባየርን ሙኒክ ወጣቱን ናግልስማን አሰናብቶ ቶማስ ቱኽልን የቀጠረው ለምን ይሆን?

ተሰናባቹ ጁሊያን ናግልስማን እና ተተኪው ቶማስ ቱኽል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተሰናባቹ ጁሊያን ናግልስማን እና ተተኪው ቶማስ ቱኽል
ታትሟል

በቅርብ ዓመታት ካየናቸው አስገራሚ ከሚባሉ የአሠልጣኞች ሹም ሽረቶች ባሳለፍነው ሳምንት ባየርን ሙኒክ ያደረገው ጎልቶ የሚወጣ ነው።

የጀመርኑ ክለብ ወጣቱ አሠልጣኝ ጁሊያን ናግልስማንን አባሮ የቀድሞውን የቼልሲ አሠልጣኝ ቶማስ ቱኽልን ቀጥሯል።

የ35 ዓመቱ አሠልጣኝ በመጀመሪያው የውድድር ዘመኑ ባየርን ሙኒክ፣ የቡንደስ ሊጋ ዋንጫን እንዲያነሳ ያደረገ ሲሆን፣ በያዝነው ዓመት ደግሞ ከዶርትመንድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

አልፎም በቻምፒዮንስ ሊግ ስምንት ጨዋታዎች አድርጎ ሁሉንም በማሸነፍ በሩብ ፍፃሜ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ተደልድሏል።

በባየርን ሙኒክ አሠልጣኝነት ዘመኑ የ2.19 ነጥብ የማሸነፍ ግምት የሚሰጠው ቡድን፣ የመሠረተው ናግልስማን በያዝነው የውድድር ዘመን ሦስት ጊዜ ብቻ ነው ሽንፈት የቀመሰው።

ይህ የማሸነፍ ክብረ ወሰን በባየር ሙኒክ አሠልጣኞች ታሪክ አራተኛው ያደርገዋል። ነገር ግን ክለቡ በውጤቱ ደስተኛ አይደለሁም ብሏል።

በቅርቡ የክለቡ ሊቀ-መንበር ኸርበርት ሃይነር፤ አሠልጣኙ ለቦታው “ትክክለኛ ሰው” ነው ሲሉ መናገራቸው አይዘነጋም።

በ2021 ከአርቢ ሊፕዚግ የመጣው አሠልጣኙ ሜዳ ላይ ለውጥ አምጥቷል አላመጣም የሚለው እንዳለ ሆኖ በመጀመሪያው ዘመኑ ሙኒክ 32ኛ ቡንደስ ሊጋ ዋንጫውን እንዲያነሳ አድርጓል።

ነገር ግን በዚያኑ ዓመት የሩብ ፍፃሜውን ማለፍ ሳይችል ቀርቷል።

ባለፈው ክረምት የክለቡን በራስ መተማመን ከፍ ለማድረግ በሚል አዳዲስ ነገሮችን ይዞ ብቅ ያለው አሠልጣኙ፣ ባየርን ከመስመር ጨዋታ ወደ መሃል እንዲያጋድል አድርጓል።

ምንም እንኳ ክለቡ አዲሱን የናግልስማን አጨዋወት ለመልመድ ጊዜ ቢወስድበትም የባየርን ቁጥር አንድ አጥቂ የሆነው ሮበርት ሌቫንደቭስኪን የሚተካ ተጫዋች እስካሁን አላገኘም።

ባየርን ከዓለም ዋንጫው በፊት 10 ጨዋታዎችን በተከታታይ አሸንፏል። ከዓለም ዋንጫው በኋላ ግን ከ10 ጨዋታዎች 12 ነጥብ ጥሏል። ይህም የቡንደስሊጋ ውድድርን አጓጊ አድርጎታል።

ጁሊያን ናግልስማን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጁሊያን ናግልስማን
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባፈለው እሑድ በባየር ሌቨርኩሰን 2 ለ 1 የተሸነፈው ባየርን፣ በቡንደስሊጋው ከዶርትመንድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንዲቀመጥ ሆኗል።

ናግልስማን በመልበሻ ክፍል ከአንዳንድ ተጫዋቾች ጋር አይስማማም።

ከእነዚህ መካከል ቀንደኛው የጀርመን እና ባየርን ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ማኑዌል ኑዌር ነው።

አሠልጣኙ እና ኑዌር ዐይን ለዐይን ተያይተው አያውቁም። ይህ ጠባቸው የከረረው ባለፈው ታኅሣሥ ኑዌር በረዶ ላይ ሊንሸራተት ሄዶ እግሩ በተሰበረበት ወቅት ነው።

ሌሎችም ተጫዋቾች በናግልስማን የአሠለጣጠን ስልት ደስተኛ እንዳልሆኑ እና አሠልጣኙ በጨዋታ ወቅት ከመስመር ውጪ የሚያሰማው ጩኸት እንደማይመቻቸው ተናግረው ያውቃሉ።

አሠልጣኙ፤ ሚስቱን ትቶ ከአንድ የጀርመን ጋዜጣ ሪፖርተር ከሆነች ሴት ጋር ግንኙነት መጀመሩ ሌላኛው በክለቡ እና በአሠልጣኙ መካከል የተፈጠረ ቁርሾ መነሻ ነው።

ባየርን ሙኒክ የአሠልጣኙ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል እያለ በሚመክርበት ወቅት ናግልስማን ከጓደኛው ጋር ለሽርሽር ኦስትሪያ ነበር።

ወጣም ወረደ ባየርን ሙኒክ ወጣቱን ውጤታማ እና ተስፋ ያለው አሠልጣኝ ማባረሩ ያልተብላላ ውሳኔ ነው ሲሉ ብዙዎች ወቀሳ አሰምተዋል።

ሙኒክ፤ 25 ሚሊዮን ዩሮ ከፍሎ ነው አሠልጣኙን በፈረንጆቹ 2021 ከአርቢ ሊፕዚግ ያስመጣው።

ናግልስማን አዲስ ክለብ እስኪያገኝ ድረስ ከባየርን ሙኒክ የሚያገኘው ክፍያ ይቀጥላል።

አዲሱ የባየርን አሠልጣኝ ጀመርናዊው ቶማስ ቱኽል፣ ባለፈው መስከረም ከቼልሲ ከተባረሩ በኋላ ያገኙት የመጀመሪያው ሥራቸው ነው።

ምንም እንኳ የ49 ዓመቱ ቱኽል የባየርን ሙኒክ አሠልጣኝ የመሆን ፍላጎት ቢኖራቸውም፣ ቦታውን እንዲህ በቀላሉ አገኘዋለሁ ብለው አስበው አያውቁም።

ከቼልሲ የተባረሩት ቱኽል በአስር ቀናት ጊዜ ውስጥ ባየርን ሙኒክን ይዘው በቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ማንቸስተር ሲቲን ለመግጠም ወደ እንግሊዝ ያመራሉ።