በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ በአንዲት ሴት ጭንቅላት ውስጥ በህይወት ያለ ትል ተገኘ

ታትሟል

በአንዲት አውስትራሊያዊት ሴት ጭንቅላት ውስጥ ርዝመቱ 8 ሴንቲሜትር የሚሆን ትል በሕይወት መገኘቱን ሳይንቲስቶች አረጋግጠዋል።

ይህም በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ያጋጠመ ክስተት መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የተረጋገጠው ታማሚዋ በአወስትራሊያ ካንቤራ በተደረገላት ቀዶ ሕክምና ላይ ነው።

ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ትሉ ቢያንስ ለሁለት ወራት የታማሚዋ ጭንቅላት ውስጥ ቆይቶ ሊሆን ይችላል።

ግለሰቧ ለወራትም ያህል በሆድ ህመም፣ ሳል፣ ላብ ላብ ማለት፣ እየጨመረ በመጣ የመርሳት እና የድባቴ ህመም ስትሰቃይ ነበር ተብሏል።

ክስተቱን ተከትሎ ተመራማሪዎች ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ሁሉም ሰው በቀዶ ሕክምና ወቅት ያልተጠበቀ ነገር ሲገጥመው ሊደነግጥ ይችላል። ነገር ግን 8 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም ትላትል ሲገኝበት ደግሞ የበለጠ ያስደነግጣል” ብለዋል ቀዶ ሕክምናውን የሰሩት የካንቤራ ሆስፒታል ሐኪም።

“ምክንያቱ ሊታወቅ ቢችልም እንኳ ይህ ክስተት በሰው ልጅ ታሪክ የመጀመሪያው ነው”

ሳይንቲስቶች በሰጡት መላምት መሰረት ሴትዮዋ ምናልባት ከባሕር ዳርቻ የሚገኝን ሳር ስትሰበስብ ትሉ ተላልፎባት ሊሆን ይችላል።

መህራብ ሆሴን የተባሉ ተመራማሪ እንደሚሉት ደግሞ በአካባቢው የሚታወቅ እባብ ያረፈበት እና ሌሎች ትላትሎች የጣሉት እንቁላል ያለበትን ሳር በመጠቀሟ የመጣ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ሴትዮ በዚህ ምክንያት የሆድ ሕመም፣ ሳል፣ ተቅማጥ እና የተባባሰ ድብርትን አስከትሎባት ነበር።

በዚሁ ሕመም ምክንያት ታማሚዋ በጎሮጎሳውያኑ 2021 ሆስፒታል ገብታለች።

ከዓመት በኋላ ደግሞ በቀዶ ሕክምና የሕመሟ መንስኤ ታውቋል።

ባለፉት 30 ዓመታት 30 የሚደርሱ የተለያያዩ አዳዲስ በሽታዎች ተመዝገበዋል።

ከእነዚህ በሽታዎች መካከል ሦስት አራተኛ የሚሆኑት ከእንስሳት ማቆያ የሚዛመቱ መሆናቸውን ባለሙያዎች አረጋግጠዋል።

ይህ ደግሞ የሰው ልጅ በተለያየ መልኩ ከእንስሳት ጋር በሚያደርገው ቀረቤታ የሚፈጠር ነው ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

“ምንም እንኳን አሁን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየቀነሰ ቢሆንም መንግሥታት እና ተመራማሪዎች ጥሩ የቅኝት መሣሪያ ማዘጋጀት አለባቸው” ብለዋል ተመራማሪዎቹ።