በአገው ታጣቂዎች ወደተያዙ የዋግ ኽምራ ቀበሌዎች የመንግሥት ሠራተኞችን ማስገባት ተጀመረ

የአገው ታጣቂ ቡድን አባላት

የፎቶው ባለመብት, ALF/FB

የምስሉ መግለጫ, የአገው ታጣቂ ቡድን አባላት
ታትሟል

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስር በሚገኙ እና በአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (አዴን) በተያዙ የአበርገሌ ወረዳ 12 ቀበሌዎች ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች በድጋሚ ማሰማራት እንደተጀመረ የአበርገሌ ወረዳ አስተዳደር እና አዴን ለቢቢሲ ገለጹ።

በሁለቱ ወገኖች ስምምነት መሠረት የአካባቢው የመንግሥት ሠራተኞች ወደ አካባቢዎቹ ቢመለሱም የቀበሌዎቹ “ፖለቲካዊ እና የፀጥታ አስተዳደር ለጊዜው” በታጣቂዎቹ ስር እንደሚቆይ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ አስታውቋል።

በዋግ ኽምራ ብሔሰረብ አስተዳደር አበርገሌ ወረዳ ውስጥ ወደሚገኙት 12 ቀበሌዎች የመንግሥት ሠራተኞችን የመመለሱ ሥራ የተጀመረው የአማራ ክልል እና አዴን በፈጸሙት የሰላም ስምምነት መሠረት መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ክፍሌ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ ከህወሓት ጎን ተሰልፎ ከመንግሥት ጋር ሲዋጋ የነበረው አዴን፤ የሰላም ስምምነት የፈጸመው ባለፈው ታኅሣሥ 13/2016 ዓ.ም. ነበር። በዚህ ስምምነት መሠረት አዴን ትጥቅ በመፍታት እና የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ በመመዝገብ “ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ትግል ብቻ” ለማካሄድ ተስማምቷል።

ባለ ሰባት ገጹ የስምምነት ሰነድ እንደሚያስረዳው የአዴን ታጣቂዎች ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች ለመከላከያ ሠራዊት የሚያስረክቡ ሲሆን፣ ይህ ሲረጋገጥ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን “የዲሞብላይዜሽን እና የምዝገባ” ሥራ ያከናውናል።

በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳዳደር፤ አበርገሌ እና ጻግብጂ ወረዳዎች ውስጥ ከሚገኙት ቀበሌዎች ውስጥ 17 ገደማው በአዴን ታጣቂዎች ስር ናቸው። 17 ቀበሌዎች ባሉት አበርገሌ ወረዳ ውስጥ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆነው በታጣቂዎች ስር የሚገኙት 12 ቀበሌዎች ናቸው።

የስምምነቱን መፈጸም ተከትሎ ከወረዳዎቹ አመራሮች ጋር ንግግር መደረጉን ለቢቢሲ የተናገሩት የአዴን ሊቀመንበር አቶ ኪሮስ ሮምሃ፤ ታጣቂዎችን ፈርተው የሸሹ የመንግሥት ሠራተኞች እና ነዋሪዎች እንዲመለሱ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል። በጻግብጂ ወረዳ ስር በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ ግን ይህ አይነቱ ተግባር አለመጀመሩን ሊቀመንበሩ ጠቅሰዋል።

በአበርገሌ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞችን ወደ ቀበሌዎቹ የመመለስ ሥራ የተጀመረው ዛሬ ሰኞ ጥር 13/2016 ዓ.ም. መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለሙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዋና አስተዳዳሪው፤ “ከስምምነቱ በኋላ የእኛ መንግሥት ‘ቀጥታ ግቡ፤ ሥራ ጀምሩ’ ብሎ አቅጣጫ ሰጥቶናል። ነገር ግን አሁንም የእነሱ ታጣቂዎች ከቀበሌዎች ብዙም [አልለቀቁም]፤ በስምምነቱ መሠረት አንድ ላይ እየተሰበሰቡ ነው ያሉት። እኛም በተስማማነው መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ገብተው ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት መቻል አለበት የሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ስለተስማማን ይህንን ተግባራዊ እያደረግን ነው” ሲሉ ወረዳው መንግሥት አገልግሎትን ለማስጀመር እየሞከረ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ አለሙ ገለጻ አሁን በቀበሌዎቹ ወደሚገኙ የሥራ መደባቸው እየተመለሱት ያሉት የመንግሥት ሠራተኞች ብዛት ከ1,300 በላይ ነው።

እነዚህ ሠራተኞች በሽሽት ሰቆጣ ከተማ ተሰብስበው መቆየታቸውን የሚያስታውሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ ከእነዚህም መካካል መምህራን፣ የጤና፣ የግብርና እንዲሁም የመሬት ባለሙያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። ከመንግሥት ሠራተኞች ባሻገር “የብልጽግና ደጋፊ” የሆኑ ግለሰቦችም በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ መቆየታቸውንም አክለዋል።

በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር በሚገኙት ቀበሌዎች የመንግሥት አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት በአካባቢዎቹ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ችግር ውስጥ ወድቀው መቆየታቸውን አቶ አለሙ ገልጸዋል።

“እነዚህ 12 ቀበሌዎች የነበሩበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነው። በትምህርት እንኳ ብንሄድ ለአራት ዓመታት ምንም ትምህርት ሳይማሩ የቆዩ ተማሪዎችን ነው አሁን እየተረከብን ያለነው። አርሶ አደሩ ግብዓት፣ ማዳበሪያ አይጠቀምም። እናቶች በህክምና አይወልዱም፣ በወባ በሽታ ምክንያት የሞተው ብዙ ሰው ነው። በጣም በችግር ውስጥ የነበሩ ቀበሌዎች ናቸው” ሲሉ በቀሌዎቹ ውስጥ ያለውን ችግር ዘርዝረዋል።

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ የመንግሥት ሠራተኞች ወደ ቀበሌዎቹ እንዲሰማሩ እየተደረገ ቢሆንም አካባቢውን የሚቆጣጠሩት ታጣቂዎች ገና አካባቢውን አልለቀቁም።

ይህንን ሀሳብ የሚጋሩት የአዴን ሊቀመንበር አቶ ኪሮስም በተመሳሳይ ሠራተኞቹ ቢመለሱም የቀበሌዎቹ “ፖለቲካዊ እና የፀጥታ አስተዳደር” በአዴን ስር እንደሚቆይ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ኪሮስ፤ “የደኅንነት ችግር እንዳይኖር ብቻ እኛ ጠብቀን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሥራቸውን እንዲጀምሩ እየተደረገ ነው። አስተዳደር ዘርፉ ትንሽ ቆይቶ የምናየው ሆኖ እነዚህ በነጻነት ሥራ እንዲጀምሩ ተደርጓል” ብለዋል።

አክለውም፤ “የእኛ ኃላፊነት የሚሆነው የሚመጡ ሠራተኞች፣ በአጠቃላይ ሕዝቡ የፀጥታ ችግር እንዳይገጥመው መጠበቅ ነው። ስለዚህ የምንሠራው የፖሊስን፣ የፀጥታን ሥራ ነው ማለት ነው፤ በኋላ ስናስረክብ እና ወደ ውይይታችን ስንገባ [የመንግሥት] የፀጥታ አካላት ይገባሉ ማለት ነው” ሲሉ በቀበሌዎቹ ውስጥ የሚኖረውን የአስተዳደር ሁኔታ አብራርተዋል።

የቀበሌዎቹ የአስተዳደር እና የፀጥታ ዘርፎች ከታጣቂዎቹ ስር የሚወጡት “ቀስ በቀስ” መሆኑን የሚገልጹት አቶ ኪሮስ፤ ይህ ከመሆኑ በፊት መከናወን ያለባቸው ተግባር መኖራቸውን አስረድተዋል። ከእነዚህ ተግባራት መካከል የአዴን ታጣቂዎችን ወደተዘጋጁ ሦስት ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ማስገባት የሚለው እንደሚገኝበት ገልጸዋል።

ሊቀመንበሩ፤ “የፖሊስ አካል፣ ሚሊሻ ወደቦታዎቹ የሚመጣ ከሆነ ግጭቶች እንዳይኖሩ የእኛ [ታጣቂዎች] ወደ ካምፕ መሰባሰብ ያስፈልጋል” በማለት በቅድሚያ ታጣቂዎቹ ወደ ማዕከል እንዲሰባሰቡ የተፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ከሦስት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የአማራ ክልል የትግራይ አዋሳኝ በሆኑ የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ የቆየው የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፤ “የአገው ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት”ን መመሥረት ግቡ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ነው።

ታጣቂ ቡድኑ ከአማራ ክልል ጋር በፈጸመው ስምምነት ላይ የፖለቲካ ጥያቄዎቹን “የክልሉን ሕግ እና አሰራር መሠረት በማድረግ” ለማቅረብ ተስማምቷል።

የአማራ ክልል ደግሞ “የቋንቋ፣ የባህል እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ የግለሰብ እና የማኅበረሰብ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት” እንደሚሰራ የስምምነት ሰነዱ ላይ ሰፍሯል።