የሩሲያን የአየር ድብደባ ተከትሎ ኔቶ ለዩክሬን የሚሰጠውን የሚሳኤል መከላከያ ሊያሳድግ ነው

ሚሳኤል

የፎቶው ባለመብት, GENERAL STAFF OF UKRAINE'S ARMED FORCES

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኪዬቭ ያደረሰችውን የሚሳኤል ጥቃት ተከትሎ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገራት ለዩክሬን የሚያደርጉትን የሚሳኤል መከላከያ ድጋፍ እንደሚያሳድጉ ገለጹ።

የኔቶ አባላት ለዩክሬን የሚሰጡት እጅግ ዘመናዊ የአየር መሣሪያ መከላከያዎች ናቸው።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ የሚለግሱት መሣሪያ ሚሳኤል እና ራዳርን ይጨምራል። አሜሪካም መሣሪያ ለመስጠት ቃል ገብታለች።

አንድ በቴክኖሎጂ የታገዘ ጀርመን ሠራሽ መሣሪያ ዩክሬን ገብቷል። አገሪቱን “ከሽብር ጥቃት” ለመከላከል የሚውል ዘመነኛ መሣሪያ ነው ብላለች ዩክሬን።

የዩክሬን አጋር የሆኑ 50 አገራት በብራሰልስ የኔቶ ዋና መቀመጫ የተገናኙ ሲሆን፣ ዩክሬን ውይይቱን “ታሪካዊ” ብላዋለች።

ሩሲያ ከ100 በላይ ሚሳኤል እንደተኮሰችና ብዙ ሰው አልባ አውሮፕላን እንደተጠቀመችም ዩክሬን ከሳለች።

ጥቃቱ በተፈጸመበት የመጀመሪያው ቀን ቢያንስ 19 ሰዎች ተገድለዋል። በበርካታ የዩክሬን ከተሞች መብራትና ውሃም ተቋርጧል።

በመዲናዋ መብራት በፈረቃ እንዲበራ ውሳኔ መተላለፉ ተገልጿል።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንዳሉት፣ ጥቃቱ ዩክሬን ላይ የተፈጸመው ከቀናት በፊት ለጋየው ድልድይ ምላሽ ነው።

ያሳለፍነው ቅዳሜ ሩሲያን ከክሬሚያ ጋር የሚያገናኘው ድልድይ ላይ ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

ፍንዳታው የተቀነባበረው በዩክሬን ነው ስትል ሩሲያ ብትከስም፣ ዩክሬን ክሱን አጣጥላለች።

ዩኬ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመለገስ የዩክሬንን የመረጃ ማሰባሰብ አቅም እንደምታጠናክርና በተጨማሪም የሚሳኤል መከላከያ 18 ሆውትዘር መሣሪያዎች እንደሰጠች ተገልጿል።

የመከላከያ ሚኒስትር ጸሐፊው ቤን ዋለስ “ሩሲያ ከሰሞኑ በንጹኃን ዜጎች ያደረሰችው ጥቃት ዩክሬን ራሷን እንድትከላከል መሣሪያ እንዲደግፋት የሚያነሳሳ ነው” ብለዋል።

የአሜሪካ የመከላከያ ጸሐፊ ሎይድ ኦስተን ከብራስልሱ ውይይት በኋላ ”ዩክሬናውያን ስኬታማ እንዲሆኑ የተቻለንን ሁሉ ከማድረግ ወደኋላ አንልም” ብለዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም አገራቸው ለዩክሬን የአየር መሣሪያ መከላከያዎች እንደምትለግስ አስታውቀዋል።

ኔዘርላንድስ 13 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሚሳኤል እንደምትሰጥ መከላከያ ሚኒስትሩ ካጅሳ ኦልንግርን ተናግረዋል።

ካናዳ በበኩሏ 34 ሚሊዮን ዶላር የሚገመቱ ሰው አልባ አውሮፕላን፣ ሳተላይትና ሌሎችም መሣሪያዎች ለመለገስ ቃል ገብታለች።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አጋሮቻቸው የአየር መሣሪያ መከላከያ እንዲሰጧቸው ለወራት ሲማጸኑ ነበር።

“የሩሲያ ጥቃት እየተባባሰ በመጣ ቁጥር ዩክሬንን መደገፍ፣ በአውሮፓ የዘመናችን ትልቁ ሰብአዊ እርዳታ ይሆናል” ሲሉ ንግግር አድርገዋል።

የዩክሬን አጋሮች የመሣሪያ ድጋፍ እንዳያደርጉ ሩሲያ ስታስጠነቅቅ ቆይታለች።